
ከሚሴ: የካቲት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ከዞን እና ከከተማ አሥተዳደር ገንዘብ መምሪያ ኀላፊዎች እና የማኔጅመንት አባላት ጋር የ2018 በጀት ዓመት የሥድስት ወር እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በከሚሴ ከተማ እያካሄደ ነው።
የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ አታላይ ጥላሁን በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሥድስት ወራት ገቢን እና ወጪን በማጣጣም ትልልቅ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል። የክልሉ በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ቢሮው የክትትል እና ድጋፍ ሥራ ማከናወኑን አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ የካፒታል በጀት ለገጠር ወረዳዎች በመመደብ እና አጋር አካላትን በማስተባበር በኩል ጥሩ አፈጻጸም እንደነበር ተናግረዋል። በቀጣይም ከመሪዎቹ እና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት በመሥራት የዲጂታል አሠራርን በማጠናከር እና የግዥ ሥርዓቱን ከሲስተም ጋር በማያያዝ በኩል በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም ባለፉት ወራት በችግርም ውስጥ ኾኖ የክልሉን በጀት በሚገባ ተግባር ላይ ለማዋል ትኩረት ተደርጎ ሲሠራ መቆየቱን ነው የጠቀሱት። የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል እና የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስተካከል በቀጣይ የሚሰጡ አቅጣጫዎችን ለመተግበር እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።
በመድረኩ በአማራ ክልል ከኹሉም ዞኖች እና ሪጆፖሊታን ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ የገንዘብ መምሪያ ኀላፊዎች እና የማኔጅመንት አባላት እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ:- ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
