በሰሜን ሸዋ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 250 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል።

6

ደብረ ብርሃን፡ የካቲት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ከተማ የ”ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት” መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሽ ዓለማየሁ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በዞኑ ውስጥ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ለመሰማራት የወሰኑ 250 አዳዲስ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ዞኑ ከ23 በላይ የሚኾኑ የተለያዩ የተፈጥሮ ማዕድናት ክምችት ያለው በመኾኑ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት የትልቅ አቅም ባለቤት ሰለመኾኑም ገልጸዋል።

በዞኑ ያለውን መሬት በአግባቡ እና በከፍተኛ ደረጃ ለማልማት እንዲቻል የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ። “ልማት ያለ ሰላም አይታሰብም” ያሉት አቶ መካሽ፣ ሕዝቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ ለኢንቨስትመንት ምቹ ኹኔታን የመፍጠር ኀላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በተለይም የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ማኅበረሰብ ድንቅ የሥራ ባሕል ባለቤት ከመኾኑም ባሻገር በትርፍ አምራችነቱም በአርዓያነት የሚታወቅ ነው ብለዋል አቶ መካሽ። መንግሥት ለባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እና ማበረታቻ እያደረገ መኾኑን በመግለጽ፣ ሌሎች አልሚዎችም ወደ ዞኑ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ዞኑ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በሚደረገው ጥረት ውስጥ በተሻለ አቋም ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሃብቶችም በፍጥነት ወደ ሥራ በመግባት ለዜጎች የሥራ እድል እንዲፈጥሩና ለኢኮኖሚው የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ተጠይቋል።

የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ የመንግሥት እና የሕዝብ የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አሥተዳዳሪው አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፦ ስንታየሁ ኃይሉ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየእናቶችን ሕይዎት ለመታደግ የባለሙያዎች እና አጋር አካላት ተሳትፎን ማጠናከር ይገባል።
Next articleየአማራ ክልልን ለኢንቨስትመንት ምቹ እና ተመራጭ ለማድረግ ስትራቴጂካዊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።