
ባሕር ዳር: የካቲት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በሰቆጣ ከተማ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የተገነባውን ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በጀግንነት ሀገር ያጸናችሁ ናችሁና እናከብራችኋለን ብለዋል። በሀገር መከላካያ ሠራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ሠራዊት አባላት በጀግንነት ሕዝብን ታድጋችኋልና እናመሰግናችኋለን ብለዋል።
መስዋዕትነት ከፍላችሁ ሀገር አቁማችኋል ነው ያሉት። ሕዝብን ከመጠበቅ ባሻገር ለሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ትልቅ ሥራ ሠርታችኋልና እናከብራችኋል ብለዋል። ለሠሩት ዲጂታል ቤተ መጻሕፍትም ምስጋና አቅርበዋል።
ሰቆጣ ከተማ የዋግሽሞች መናገሻ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያላት መኾኗንም ገልጸዋል። ሕዝቡም ለኢትዮጵያ አንድነት የጸና ታማኝ እና ባለታሪክ መኾኑን ተናግረዋል።
ጽንፈኝነትን በመታገል በሰላም እየኖረ ያለ አስተዋይ እና ጀግና ሕዝብ መኾኑንም አንስተዋል። የአካባቢው ተወላጆች፣ ባለሃብቶች እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን በከተማዋ ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ሌትናል ጄኔራል ዘውዱ በላይ ሠራዊቱ ከወር ገቢው አዋጥቶ ቤተ መጻሕፍቱን መገንባቱን ገልጸዋል።
ለጀግና መታሰቢያ ሐውልት ነው፤ እኛ ግን ለሀገር እና ለሕዝብ ሲሉ መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች መታሰቢያ ሐውልቱ ቤተ መጻሕፍት እንዲኾን ወስነናል ነው ያሉት።
ሀገራችን የተሻለ አስተሳሰብ ያላቸው ልጆች እንዲፈጠሩላት ዘመናዊ እና ዘመኑን የዋጀ ቤተ መጻሕፍት ገንበተናል ብለዋል። ዋና ተልዕኳችን ሰላምን መገንባት ነው ያሉት አዛዡ ቤተ መጻሕፍት የገነባነውም ሥልጣንን በኃይል የመያዝ አባዜ አብቅቶ በሃሳብ የበላይነት ማመን እንዲመጣ ነው ብለዋል።
እኛ ያሸነፍነው ጽንፈኝነት እና የእብሪት አስተሳሰብን ነው፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጽንፈኝነትን፣ ከእኔ በላይ ጦር የሚችል የሚል እብሪተኛን ድል በማድረግ ሀገር ማጽናቱን ተናግረዋል።
ጦርነት ይበቃናል፣ ለሰላም እንሥራ ነው ያሉት። ሠራዊቱ በግዳጅ ተወጥሯል በሚል የተሳሳተ አመለካከት ግጭት ለማንሣት የሚሠራ አለ፤ ነገር ግን ሠራዊቱን በቀጣናው የሚያቆም ኃይል የለም፤ ሠራዊቱ ሀገርን የሚያኮራ፤ ለሀገሩ የቆመ ጀግና ነው ብለዋል።
ለሰላም መሥራት ይሻላል፤ በተሳሳተ ግምገማ ሠራዊቱን መንካት የከፋ ጉዳት ያደርሳል፣ ዋጋም ያስከፍላል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
