
ደሴ: የካቲት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ለሦስተኛ ጊዜ ሀገራዊ የምርምር ጉባኤን እያካሄደ ነው። በጉባኤው ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።
አሚኮ ያነጋገራቸው ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ጥናት አቅራቢዎች እና ተጋባዥ እንግዶች ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎችን ከተለያዩ ቦታዎች ጋብዞ የልምድ ልውውጥ ማድረጉ ለወጣት ተመራማሪዎች ልምድ እንደሚያስገኝ አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለግብርና እና ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠው ትኩረት የሚበረታታ መኾኑንም ተናግረዋል። ወደ ማኅበረሰቡ የሚወርዱ ተጨባጭ ሥራዎች ላይ በትኩረት መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።
የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምርምር፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ስለሺ አቢ (ዶ.ር) ታሪካዊውን የምርምር ኮንፈረንስ ለሦስተኛ ጊዜ ማዘጋጀታቸውን አንስተዋል።
አጠቃላይ ከቀረቡት ከ200 በላይ የምርምር ሥራዎች ውስጥ ለዩኒቨርሲቲው የትኩረት አቅጣጫ የሚያግዙትን 36 ጥናቶች መርጠን በኮንፈረንሱ እንዲቀርቡ አድርገናል ነው ያሉት።
መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመበት ቦታ በታሪክ እና በቱሪዝም የበለጸገ ስለኾነ በእነዚህ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ኮንፈረንሱ ከተለያዩ ተመራማሪዎች ተሞክሮዎችን እና ልምድ ለመቅሰም ያግዘናልም ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምር፣ ሕትመት እና ሥነ-ምግባር ሥርጸት ዳይሬክተር አገኝ ሽበሽ (ዶ.ር) ተመራማሪዎች የተለያየ ልምድ እና ዕውቀት ይዘው መምጣታቸው የዕውቀት እና የልምድ ልውውጥ እንዲደረግ ያስችላል ብለዋል። ይህም የምርምር ሥራዎቻችን ጥራት ያላቸው እንዲኾኑ ያግዛል ነው ያሉት።
ኮንፈረንሱ መካሄዱ “የመማር ማስተማር እንቅስቃሴውን በምርምር የተደገፈ” ለማድረግ እና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት እንደሚያግዝም ገልጸዋል።
የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የአሥተዳደር እና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ሰዋገኝ አሥራት (ዶ.ር) ኮንፈረንሱ አካባቢውን በማስተዋወቅ የገጽታ ግንባታ ሥራ መሥራት ዓለማ ማድረጉን ተናግረዋል።
ዩኒቨርስቲው የተቋቋመበት ቦታ እምቅ ሀብት ያለበት እንደመኾኑ የዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ ብቻ ሳይኾን የትኛውም አካባቢ ያለ ተመራማሪ የምርምር ሥራዎችን ማጥናት እንደሚችል ለማሳየት መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- መስዑድ ጀማል
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
