
አዲስ አበባ: የካቲት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ሥልጠና ምዘና ውድድር “የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልዕክት በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ውድድር ከ15 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊወችን የሚያወዳድር ሲኾን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በውድድሩ ማስጀመሪ መርሐ ግብር የክብር እንግዳ ኾነው የተገኙት የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሼዊት ሻንካ ዛሬ የምናካሂደው የመጀመሪያው የታዳጊዎች ሀገር አቀፍ ውድድር መንግሥት ለስፖርት ልማት የሰጠውን ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋልብ። በታዳጊ እና “ተተኪ ወጣቶች ላይ መሥራት ለነገ ስፖርት ስኬት መሠረት መጣል መኾኑንም” አንስተዋል።
ይህ ውድድር ታዳጊዎች ብቃታቸውን የሚመዝኑበት እና ተሰጥኦዋቸውን ለሀገር የሚያሳዩበት ወሳኝ መድረክ ነውም ብለዋል። ይህ ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ ያለው ውድድር ከግብ ሊደርስ የሚችለው የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ እና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሲታከልበት መኾኑን ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ ስፖርት ዘላቂ እድገት እና ለውጥ በታዳጊዎች ሥልጠና እና ውድድር ውስጥ የሚታይ ቅንጅት ፋይዳው እጅግ የጎላ መኾኑንም የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሼዊት ሻንካ ገልጸዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከስፖርት ልማት ዘርፍ በሚጠበቀው ልክ ጥቅም ሳታገኝ መቆየቷን ያነሱት የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ ሮዛ አባቢያ ናቸው። አሁን ላይ የፖሊሲ እና የሕግ ማቀፍ በማበጀት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል። ውድድሩ የማይረሳ እና የምተደስቱበት እንዲኾን እመኛለሁ የሚል መልዕክትም ለተሳታፊወች አስተላልፈዋል::
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የአዳማ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ኃይሉ ጀልዱ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
