ምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የቡና ምርትን ለማሳደግ እየሠራ ነው።

9

8ደብረ ማርቆስ: የካቲት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በተመረጡ ወረዳዎች የቡና ምርትን በስፋት ለማልማት በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ አስታውቋል።

በቡና አብቃይ ወረዳዎች በእያንዳንዳቸው አንድ ቀበሌ በመለየት 50 ሄክታር መሬት ላይ ቡናን ለማልማት ትኩረት ያደረገ ሥራም ተጀምሯል።

ተግባሩ ባሶ ሊበን፣ ጎዛምን፣ ማቻከል እና ደብረ ኤሊያስ ወረዳዎችን ያካተተ ሲኾን በዘርፉ የአርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን የተናገሩት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አበበ መኮንን ናቸው።

ቡና የሚያለሙ አርሶ አደሮችን የመለየት እና የማሠልጠን ሥራ እየተከናወነ ስለመኾኑም አቶ አበበ ገልጸዋል።

የጎዛምን ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሀብታሙ ይታይህ በወረዳው ቡናን የማልማት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ብለዋል። በ14 ቀበሌዎች ውስጥ 400 ሄክታር መሬት በቡና ችግኝ የለማ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

በወረዳው በሚገኙ ችግኝ ጣቢያዎች ከ120 ሺህ በላይ የቡና ችግኝ በማፍላትም ለቀጣይ ተከላ ለማሠራጨት እየተሠራ ነው ብለዋል። በዚህ ዓመት እስካሁን የተሰበሰበ ከ200 ኩንታል በላይ ቡና እንዳለ የገለጹት ኀላፊው የገበያ ትስስር ለመፍጠርም ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑ አንስተዋል።

በዞኑ ለአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ የደን እና የመኖ ችግኝ ልማት ከ267 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለማልማት እንደታቀደ ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

እስካሁን ከ58 ሚሊዮን በላይ ችግኝ የተፈላ ሲኾን ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የሚኾነው የቡና እና የፍራፍሬ ችግኝ እንደኾነም መረጃው ያመላክታል።

አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article👉 ደራሲ አቤ ጉበኛ (1925 ዓ.ም -1972 ዓ.ም)
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በሰቆጣ ከተማ የተገነባውን ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት መርቀው ሥራ አስጀመሩ።