
ባሕር ዳር: የካቲት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ደራሲ አቤ ጉበኛ በአማራ ክልል ጎጃም አቸፈር ወረዳ ልዩ ስሙ ኮረንች አቦ በተባለ ቀበሌ በ1925 ዓ.ም ነው የተወለደው፡፡ ደራሲ አቤ ጉበኛ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ከመኾን በተጨማሪ ሀገሩን በማስታወቂያ ሚኒስተርነት አገልግሏል።
በደልን እና ብልሹ አሠራርን በብዕሩ የሚታገል ደፋር ደራሲም እንደነበር የሕይወት ታሪኩ ያሳያል። ደራሲ እና ጋዜጠኛ አቤ ጉበኛ ከ27 በላይ መጻሕፍትን በመጻፍ ትልቅ አበርክቶ ያለው ሰው ነው። በተለይም አልወለድም፣ ሰይፈ ነበልባል እና የአመጽ ኑዛዜ ከመጻሕፍቶቹ ይጠቀሳሉ።
ደራሲ እና ጋዜጠኛ አቤ ጉበኛ በ47 ዓመቱ በዚህ ሳምንት የካቲት 01/1972 ዓ.ም ነው ያረፈው።
ምንጭ፦ በጋዜጠኛ እና ደራሲ አያልነህ ሙላቱ የተዘጋጀ “አቤ ጉበኛ ሕይወቱ እና ሥራዎቹ” መጽሐፍ።
👉 የአፍሪካ ጉዳዮች የሚመከሩበት ታሪካዊ ስፍራ
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) እና የአፍሪካ አዳራሽ ጥር 29 /1953 ዓ.ም በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ነው የተመረቁት። ሕንጻዎቹ በአዲስ አበባ ካዛንቺስ ውስጥ በ55 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ ናቸው።
በ6 ሚሊዮን ብር የተገነቡት ሕንጻዎቹ በአርክቴክትነት ኢትዮጵያዊው ኢንጂነር ጌታቸው ማህተመሥላሴ ተሳትፈውበታል። የአፍሪካ ጉዳዮች የሚመከሩበት ታሪካዊ ስፍራም ነው።
የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን 3ኛውን ጠቅላላ ስብሰባ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደውም በዚህ አዳራሽ ነው።
ምንጭ፦ በብላቴን ጌታ ማሕተመሥላሴ ወልደመስቀል የተጻፈው “ታሪክ እና ምስክር” መጸሐፍ።
👉የሬጌው ንጉሥ ቦብ ማርሌ (ሮበርት ኔስታ ማርሌይ)
የሬጌው ንጉሥ ቦብ ማርሌ በዚህ ሳምንት ጥር 29/1937 ዓ.ም ነው በጃማይካ የተወለደው። ቦብ ማርሌ “ዘ ዋይለርስ” የተባለውን ታዋቂ ቡድን በመመሥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሬጌ ሙዚቃን አስፋፍቷል።
ቦብ ማርሌ ለኢትዮጵያ ጥልቅ ፍቅር እና አክብሮት የነበረው ሰው ነው። ከሙዚቃ ውጭ ለእግር ኳስ ስፖርትም ከፍተኛ ፍቅር እና ተሰጥኦ እንደነበረው ይነገራል።
በአጭር የሕይወት ዘመኑም ዓለምን ያዳረሱ እና እስከ ዛሬ የሚዘመሩ የሰላም፣ የአንድነት እና የነጻነት ሙዚቃዎችን ጥሎ አልፏል።
ምንጭ፦ “Catch a Fire: The Life of Bob Marley” በቲሞቲ ኋይት የተጻፈ መጽሐፍ።
በምሥጋናው ብርሃኔ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
