“የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ለአካባቢው ግርማ ሞገስን ያላበሰ፣ ለእኛም ሃሴትን የሞላ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

3
ባሕር ዳር፡ ጥር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሎጎ ሐይቅ ሪዞርትን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በመረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ይህ ሪዞርት ለሆቴል የሚሰጠው አገልግሎት እንደተጠበቀ ኾኖ ለክልሉ ልማት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የተገነባበት አካባቢ ከአዲስ አበባ የታላቁ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ጀምሮ ለዓድዋ ድል ክተት የታወጀበት ወረኢሉን፣ የውጫሌ ውል የተሰናዳበትን ይስማ ንጉሥን፣ ማይጨውን እና የጥቁር ሕዝቦች የድል አድራጊነት ምልክት የኾነውን ዓድዋን የሚያስተሳስር፣ የቱሪስት ፍሰት መስመር ኾኖ የሚያገለግል መኾኑን ነው የተናገሩት።
ሪዞርቱ የተገነባበት አካባቢ እድሜ ጠገብ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊ እና ታሪካዊ የቱሪስት መስህቦች እንዳሉትም ገልጸዋል። በቱሪዝም መዳረሻ ልማት ችግር ምክንያት ለቱሪስት ባይተዋር ኾነው የቆዩትን አካባቢዎች ተደራሽ የሚያደርግ መኾኑንም ተናግረዋል። ከተሞችን የሚያስተሳስር የልማት አቅም መኾኑንም ገልጸዋል።
በክልሉ መዋለ ነዋያቸውን ለሚያፈስሱ ባለሃብቶች፣ የሀገርን ገጽታ እና የሀገርን ክብር ከፍ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች በአካባቢው ለመገንባት እንዲችሉ ምሳሌ እና የስበት ማዕከል ኾኖ እንደሚያገለግል አንስተዋል።
“ለአካባቢው ግርማ ሞገስን ያላበሰ፣ ለእኛም ሃሴትን የሞላ ፕሮጀክትም ነው” ብለዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገሪቱን ያደረሱ፣ የመልማት ጸጋችንን የዳሰሱ ፕሮጀክቶች በሚያስገርም ፍጥነት እና ጥራት እንዲጠናቀቁ ያደረጋቸው በልማት ላይ ያተኮሩ ዐይኖች፤ መበልጸግን የሚያሰላስል የልቦና ውቅር፤ በጎ መሥራትን የሚያስቡ አዕምሮዎች ናቸው ብለዋል።
የዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ የኾነው አስተሳሰብ እና ተግባር ደግሞ ጦርነት እስከ መቃብር ብሎ አፈር ከለበሱ ብረቶች ጋር ተሟሙቶ ይውላል ነው ያሉት። የመንግሥት ቀናኢ የልማት ፍላጎት ብቻውን ውጤታማ እንደማይኾን የሎጎ ሐይቅ ማሳያ መኾኑንም ገልጸዋል።
የመንግሥትን በጎ እሳቤ ተረድቶ፣ ሌሎች በዓድ ፍላጎቶችን ገርቶ፣ ሌት ከቀን የሚተጋ ባለሃብት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
በጎ ተግባርን የሚደግፍ ሕዝብ ሲኖር ደግሞ በፍጥነት እና በጥራት፣ በፈጠራ እና በውጤት እንዲህ አይነት ፕሮጄክቶች ይፈጸማሉ ነው ያሉት። ፕሮጄክቱ ውብ ኾኖ እንዲሠራ ላደረጉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበትምህርት ላይ የደረሰውን ስብራት ለመጠገን በቁጭት መሥራት ይገባል።