
ባሕር ዳር: ጥር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ይህ ሥፍራ የረቀቀው ታሪክ ታትሞበታል፤ ይህ ሥፍራ ለዘመናት ዕውቀት እንደ ዥረት ፈስሶበታል፤ እንደ ሐይቁ ጥልቅ ኾኖ ኖሮበታል፤ ይህ ሥፍራ ሃይማኖት ለዘመናት ተሰብኮበታል፤ ዘመንን በጥበብ ክንድ የለኩ ብጹዓን ተመላልሰውበታል።
ሐይቅ ባርከው በረከት አዝንበውበታል፤ ክፉውን አውግዘው መልካሙን አትመውበታል፤ ደግነት እንዲበዛ ክፋት እንዲጠፋ መሠረት አጽንተውበታል።
በዚህ ሥፍራ ሊቃውንት እንደ ማለዳ ጮራ እያበሩ ወጥተውበታል፤ እንደ ጀንበር ደምቀው ኖረውበታል፤ የጨለመውን ዘመን በዕውቀታቸው ብርሃን ገልጠውበታል፤ የተጣመመውን መንገድ በጥበባቸው ልኬታ አስተካክለውበታል፡፡
በዚህ ሥፍራ ዓለምን የናቁ አበው ያለማቋረጥ ተመላልሰውበታል፤ በሐይቅ ላይ የሚመላለሱ ስውራን በጥበብ እና በንጽሕና ኖረውበታል፤ ከሰው ተለይተው ስለ ሀገር እና ስለ ሕዝብ ጸልየውበታል፤ ዛሬም ይጸልዩበታል።
ይህን ሥፍራ አቡነ ኢየሱስ ሞአ በቅድስና በመስቀላቸው ቀድሰውታል፤ በዘንጋቸው ባርከውታል፤ እርሳቸው የተመረኮዙባት፣ ዘመንን የለኩባት፣ ከትናንት ወዲያ ኾነው ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን ያስተሳሰሩባት በትረ ሙሴያቸው ዛሬም ትባርካለች፤ ዛሬም የትናንቱን ታሪክ ትናገራለች፤ የቀደመውን ትመሰክራለች፡፡
በዚህ ሥፍራ ጳጳሳቱ እና ሊቃውንቱ ያለማቋረጥ ስብሐተ እግዚአብሔር ያደርሱበታል፤ ነገሥታቱ እና መኳንንቱ እጅ ነስተውበታል፤ ለክብሩ የተገባውን፣ ለግርማው የሚኾነውን፣ ለቅድስና የሚሰጠውን ስጦታ አቅርበውበታል፤ ዘመናቸው የተባረከች ትኾን ዘንድ ተማጽነውበታል፤ ቃል ኪዳንም አጽንተውበታል ሐይቅ እስጢፋኖስ (ሎጎ ሐይቅ)፡፡
ሐይቅ እስጢፋኖስ (ሎጎ ሐይቅ) ጮራ ነው ዕውቀት የበራበት፤ ጨለማ የተገፈፈበት፤ የጥበብ ማዕድ ነው ትውልድ ሁሉ የተቋደሰበት፣ የማይነጥፍ ዥረት ነው ጥበብ የተቀዳበት፤ ጉባኤ ቤት ነው ሊቃውንት እና ደቀመዛሙርት የማይጠፉበት፤ ከጥንት የነበረው ዕውቀት ሳይበረዝ እና ሳይከለስ የሚነገርበት፤ በዓት ነው መነኮሳቱ ዘግተው የሚኖሩበት፤ ብራና ነው የትናንት ታሪክ የሚነበብበት፤ ቁልፍ ነው ምስጢር የሚፈታበት፤ ያማረ ጎዳና ነው ትውልድ ሁሉ የሚጓዝበት፤ ሐይቅ እስጢፋኖስ ማዕዘን ነው የኢትዮጵያ የጥበብ ታሪክ የጸናበት።
ሐይቅ እስጢፍኖስ መሠረት ነው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት አሐዱ ያለበት፤ ጣሪያ ነው ሀገር የክብር ጥላ የዘረጋችበት፤ ካባ ነው ኢትዮጵያ በጥበብ የተጎናጸፈችበት፣ በትረ ሙሴ ነው ኢትዮጵያ የጨለማውን ባሕር በዕውቀት የተሻገረችበት፤ ብእር ነው የኢትዮጵያ ታሪክ የተጻፈበት፤ ቀለም ነው ኢትዮጵያዊነት ኅብረ ብሔራዊ ኾኖ የተሰቀለመበት፤ ሰገነት ነው ኢትዮጵያ ከፍ ከፍ ያለችበት፤ አድባር ነው ሀገር የሚከበርበት፡፡
ይህ አስቀድሞ የከበረው፣ ጥበብ የወረደበት፣ ዕውቀት የሰፋበት ታላቅ ሥፍራ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የከበረ ቦታ አለው፡፡ በቤተ ክህነቱም ኾነ በቤተ መንግሥቱም አሻራው ታላቅ ነው፡፡ አስተዋጽዖውም ኃይል ነው፡፡ ታዲያ ይህ አስቀድሞ ሥልጣኔ የበራበት፣ ዕውቀት እንደ ቀትር ፀሐይ የደመቀበት፤ ታሪክ እና ሃይማኖት ከፍ ብለው የተከተቡበት ሥፍራ በዘመናት መካከል እንደተነሳ፣ በዘመናት መካከልም ተረስቶ ነበር፡፡
እኒያ ታሪክ የሠሩበት፣ ሃይማኖትን ያጸኑበት፣ ጥበብን ያተሙበት ቅዱሳኑ፣ ነገሥታቱ እና ሊቃውንቱ ተዘንግተው፣ ታላቁ ሥፍራ ተረስቶ ዓመታት እንደዋዛ አልፈዋል፡፡ ዘመናት እንደዘበት ተከታትለው ነጉደዋል፡፡ ታላቁ ታሪክ እንደ ዋዛ እየተነገረ፣ አስደናቂው ውበት በዝምታ እየታየ ዓመታት ዓመታትን አስከትለዋል።
ቅዱስ እስጢፋኖስን ከብቦ የያዘው፣ ውበትን የታደለው ሐይቅ ያማረው ውበቱ ተገልጦ ለዓለም ሳይታይለት፤ ያቀፈው ታሪክ ተገልጦ ሳይነበብለት፤ ያከማቸው ጥበብ ሳይመረመርለት፤ የሰበሰበሰው በረከት ሳይገለጥለት ዓመታት አልፈው ነበር፡፡ ታሪኩን አስሰው፣ ጥበቡን ፈልገው፣ ዕውቀቱን ሽተው የሚመጡ ብልሆች እስኪመጡ ድረስ ጊዜ ለኩሉ እያለ ይጠባበቅ ነበር፡፡
ለሁሉ ዘመን አለው፡፡ ከሰማይ በታችም ለኾነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፡፡ ለመፈለግ ጊዜ አለው። ለማጥፋትም ጊዜ አለው፡፡ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፡፡ ለመጣልም ጊዜ አለው፡፡ ለመቅደድ ጊዜ አለው፡፡ ለመስፋትም ጊዜ አለው፡፡ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፡፡ ለመናገርም ጊዜ አለው፡፡ ለመውደድ ጊዜ አለው፣ ለመጥላትም ጊዜ አለው እንዳለ መጽሐፍ ለሁሉም ጊዜ አለውና ታሪክ የሚያስታውሱ፣ የትናንቱን የሚያወሱ፣ የተደበቀውን የሚገልጡ፣ የተረሳውን የሚያወጡ ብልህ ልጆች እስኪመጡ ድረስ የጠበቀው ሐይቅ እስጢፋኖስ ዛሬ ላይ ብልሆች አይተውታል፤ ዘመን ገልጦታል፤ ውበቱም ተገልጦለታል፡፡
አሁን የሎጎ ሐይቅ ውበት ተገልጧል፤ አሁን ለክብሩ የሚመጥን ሥራ ተሠርቶለታል፡፡ በገበታ ለትውልድ ለትውልድ የተገነባው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ከጥንትም በተፈጥሮ ለተሞሸረው፤ በታሪክ ለተከበረው፤ በውበት ለተንቆጠቆተው ሥፍራ ከውበት ላይ ውበት ሰጥቶታል፣ ከግርማ ላይ ግርማ ደርቦለታል፡፡
ለወትሮው እንግዳ መቀበል የማይታክቱት፣ ደግነትን ገንዘባቸው አድርገው የሚኖሩት ወሎየዎች እንግዳ የሚቀበሉበት፣ ያልተበረዘውን ውበታቸውን፣ የሚያስቀናውን ፍቅራቸውን፣ የሚያስደንቀውን ደግነታቸውን፣ የሚያስገርመውን እንግዳ ተቀባይነታቸውን፣ የሚያሳሳውን አብሮነታቸውን በአንድ ላይ ያሳዩበታል፡፡ ይህ ሥራ ድንቅ ነው፡፡
አሁን የተደበቀው ታስሷል፣ የተረሳውም አስታዋሽ አግኝቷል፡፡ በሐይቁ ዳርቻ ኾነው የትናንቱን እያስታወሱ ሲተክዙበት የነበሩት የሕይቅ ነዋሪዎችም ዛሬ ላይ የሚተክዙበት አይደለም፡፡ ይልቅስ ትናንትን የሚናገርቡት፣ ዛሬን የሚያዩበት፣ ነገን የሚያሳምሩበት ነው፡፡ አሁን ሐይቅ ፈክታለች፣ ባማረው ሥራ ደምቃለች፡፡ ከውበት ላይ ውበት ደራርባ ተጎናጽፋለች፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
