በምሥራቅ ጠለምት ወረዳ ዲማ ከተማ የሕወሃትን ትንኮሳ የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሄደ።

5
ደባርቅ: ጥር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሕወሃት ያደረገውን የዳግም ወረራ ሙከራ የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በሰሜን ጎንደር ዞን ምሥራቅ ጠለምት ወረዳ ዲማ ከተማ ተካሂዷል።
ጥር 18/2018 ዓ.ም ሕወሃት በደገብራይ፣ ምጫራ፣ ማኅበረ እና ማይዳጉሳ በተባሉ የወረዳው አራት ቀበሌዎች የጥቃት ሙከራ ማድረጉን ተከትሎ የቡድኑን ጸብ አጫሪ ትንኮሳ የሚያወግዝ ሰልፍ ነው የተካሄደው።
በሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የምሥራቅ ጠለምት ወረዳ አሥተዳዳሪ ሲሳይ ተረፈ ሕወሃት ከጥፋት ታሪኩ ሳይማር ተደጋጋሚ የጥፋት ሙከራ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በወረዳው በሚገኙ አራት ቀበሌዎች የፈጸመው የጸብ አጫሪነት ተግባር የቡድኑ እኩይ ዓላማ አንድ መገለጫ መኾኑንም አመላክተዋል።
ቡድኑ መንግሥት ለሰላም ቁርጠኛ በመኾን ያሳየውን ትዕግስት ባልተገባ መንገድ በመረዳት በእብሪት የዳግም ወረራ ሙከራ ማድረጉን ተናግረዋል።
ለዚህም የጥፋት ሙከራ በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ የጸጥታ መዋቅር እና በማኅበረሰቡ ቅንጂት አመርቂ እርምጃ ተወስዶበታል ብለዋል። ማኅበረሰቡ ለጸጥታ መዋቅሩ ያለውን ደጀንነት በተግባር ያረጋገጠበት ክስተት እንደነበርም አብራርተዋል።
ግልጽ ባልኾነ የፖለቲካ አጀንዳ በመታለል ወደ ቡድኑ የትጥቅ ትግል የገቡ የወረዳው ነዋሪዎች ወደ ሰላም አማራጭ ሊመጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ለዚህም መንግሥት ቁርጠኛ ኾኖ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሰልፉ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶችም የሰላም ዋጋው የማይተመን እና ሁሉንም አካል ተጠቃሚ የሚያደርግ በመኾኑ ሕወሃት ከጸብ አጫሪነት ትንኮሳ ወጥቶ ወደ ሰላም እንዲመጣ ጥሪ አቅርበዋል። ቡድኑ የሚያደርገውን ማንነት ተኮር ጥቃት እንዲያቆምም አሳስበዋል።
የሰልፉ ተሳታፊ ተማሪዎች ሰላም እንዲሰፍን እና መደበኛ የትምህርት እንቅስቃሴ እንዲጀመር ጠይቀዋል።
ቡድኑ በሚያደርገው የጥፋት ትንኮሳ እየደረሰ ያለው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ቀላል የሚባል ባለመኾኑ ይሄን ሁለንተናዊ ውድመት ለማስቆም ሰላም ብቸኛ አማራጭ መኾኑንም አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“በሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት በትኩረት እየተዘጋጀን ነው” ተማሪዎች
Next article“የተረሳው ታወሰ፤ የተደበቀው ታሰሰ”