“በሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት በትኩረት እየተዘጋጀን ነው” ተማሪዎች

4
ሰቆጣ: ጥር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ አስታውቋል።
ተማሪ ኤፍሬም ኃይሌ እና ተማሪ ወርቅነሽ ንጉሴ የ12ኛ ክፈል ተማሪዎች ናቸው። ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምረው በደረጃ እየተሸለሙ የመጡ መኾናቸውን የሚያስታውሱት ተማሪዎቹ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ዋና ዕቅዳቸው እንደኾነ ተናግረዋል።
“በሀገር አቀፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ለማምጣት በትኩረት እየተዘጋጀን ነው”ብለዋል። ለዚህም በቡድን እና በተናጥል እየተዘጋጁ መኾኑንም ነግረውናል። መምህራኑም በየምዕራፉ ከ30 በላይ ጥያቄዎችን እያወጡ ይመዝኑናል ነው ያሉት።
ባለፈው ዓመት በትምህርት ቤቱ የተመዘገበው የተማሪዎች የማለፍ ቁጥር መጨመር መምህራን በተነሳሽነት ስሜት እንዲያስተምሩ እንዳገዛቸው የተናገሩት ደግሞ የመሽሃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፊዚክስ አስተማሪው መምህር ጌትነት ተስፋው ናቸው።
ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ ለተማሪዎቻቸው እያደረጉ መኾኑን ተናግረዋል።
የመሽሃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ደሳለኝ ቢምረው በተያዘው ዓመት በተፈጥሮ እና በማኅበራዊ ሳይንስ 202 ተማሪዎችን ተቀብለው ለሀገር አቀፍ ፈተና እየተዘጋጁ መኾናቸውን ገልጸዋል። ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ትምህርት ቤቱ የአዳር ጥናት እና የተደራጀ ቤተ መጻሕፍት ማዘጋጀታቸውንም ገልጸውልናል።
በስሃላ ሰየምት ወረዳ ባለፈው ዓመት ከተፈተኑ 480 ተማሪዎች ውስጥ ሪሚድያልን ጨምሮ 50 ተማሪዎች ማለፋቸውን ያስታወሱት የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ገብረሕይወት ጣፈጠ ናቸው። በ2018 ዓ.ም 395 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
ከባለፈው ዓመት የማለፍ ምጣኔ 20 በመቶ የበለጠ የተማሪ ቁጥር ለማሳለፍ አቅደው እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በዋግ ኽምራ 3 ሺህ 396 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መኾናቸውን የተናገሩት ደግሞ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ፍታለሽ ምሕረቴ ናቸው።
ለተማሪዎችም አስፈላጊውን የመጽሐፍት አቅርቦት ከማሟላት ባሻገር የአዳር ጥናት በተደራጀ መንገድ እንዲሰጥ መምሪያው ድጋፍ እና ክትትል እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ተማሪዎችም በሀገር አቀፍ እና ለክልል አቀፍ ፈተናዎች ላይ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ምክትል ኀላፊዋ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleወሎን የገለጠው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት
Next articleበምሥራቅ ጠለምት ወረዳ ዲማ ከተማ የሕወሃትን ትንኮሳ የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሄደ።