
እንጅባራ: ጥር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2018 በጀት ዓመት ከመደበኛ እና ከአገልግሎት ገቢ ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሠብሠብ ታቅዶ ሢሠራ ቆይቷል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ያለፉትን ስድስት ወራት አፈጻጸም እና በቀሪ ወራት ተግባራት ላይ ያተኮረ ግምገማ በእንጅባራ ከተማ አካሂዷል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራትም ከታቀደው የገቢ ዕቅድ ውስጥ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚኾነው ገቢ ተሠብሥቧል።
የተሠበሠበው ገቢ በበጀት ዓመቱ ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ 44 ነጥብ 9 በመቶ ነው። የግማሽ ዓመቱ 89 ነጥብ 8 በመቶ እንደኾነም ተገልጿል።
በግምገማ መድረኩ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ ገቢ የሀገር ህልውና ማስቀጠያ እና የኢኮኖሚ እድገት ማሳለጫ ቁልፍ መሣሪያ መኾኑን ተናግረዋል።
በየደረጃው ያሉ የገቢ ሠብሣቢ ተቋማት ይህንን ታላቅ ሀገራዊ ግብ ተረድተው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት። ባለፉት ስድስት ወራት የተሠበሠበው ገቢ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የገቢ አሠባሠብ ታሪክ የመጀመሪያው እና ከፍተኛው እንደኾነም አንስተዋል።
ይህንን ላሳኩ በየደረጃው ላሉ የገቢ ሠብሣቢ ተቋማት እና ተግባሩን ለመሩ የሥራ ኀላፊዎችም ምስጋና አቅርበዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ፈጠነ ጥላሁን ባለፉት ስድስት ወራት የተሠበሠበው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ722 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
የሰላም ሁኔታው እየተሻሻለ መምጣቱ፣ በየደረጃው ያሉ የገቢ ሠብሣቢ ተቋማት እና የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ለተግባሩ የሰጡት ትኩረት እና በገቢ ግብር አዋጁ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ እገዛ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
በቀሪ ወራትም በወረዳዎች መካከል ያለውን የአፈጻጸም ልዩነት በማቀራረብ በዓመቱ የተያዘውን የገቢ ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል ስምሪት ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- ሳሙኤል አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
