ሕወሀት የሰላም ስምምነቱን በመጣስ ያደረገው የጥፋት ሙከራ የቡድኑን እኩይ ተልዕኮ ያሳየ መኾኑን ሰላማዊ ሰልፈኞች ተናገሩ።

7

 

ደባርቅ፡ ጥር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ኢትዮጵያን ገንብተን እንጂ አፍርሰን አናልፍም” በሚል መሪ መልዕከት ሕወሓት እያደረገ ያለውን የዳግም ወረራ ሙከራ የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ ሕወሓት ባለፉት ጊዜያት ሲፈጽማቸው የቆዩ እኩይ ተግባራት የሚወገዙ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ሕወሓት ከትናንት የጥፋት ታሪኩ ሳይማር በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ጥቃት ለማድረስ መሞከሩንም አንስተዋል።

ጥር 18/2018 ዓ.ም ቡድኑ በጠለምት ወረዳ በኩል በአራት ግንባሮች የውጊያ ሙከራ ያደረገ ቢኾንም በመከላከያ ሠራዊት፣ በክልሉ የጸጥታ መዋቅር አባላት እና በአካባቢው ማኅበረሰብ የተቀናጀ ርምጃ ጥቃት ደርሶበታል ብለዋል።

የደባርቅ ከተማ ከንቲባ ጌትነት ጸጋዬ በበኩላቸው ሕወሓት ከጥፋት ታሪኩ ሳይማር ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በጋራ በመሥራት ኢትዮጵያን የማፍረስ እኩይ ተልዕኮውን አጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።

የአማራ ሕዝብን ዘላቂ ሰላም እና የልማት ጉዞ ለማደናቀፍ ከሚሠሩ ጽንፈኞች ጋር በመሥራትም የጥፋት ተልዕኮውን በተዘዋዋሪ ለማስፈጸም ሙከራ ሲያደርግ መቆዬቱንም አብራርተዋል።

የደባርቅ ወረዳ አሥተዳዳሪ ሰለሞን ጌትነት በበኩላቸው ሕወሓት በዳግም ወረራ የሰላም ስምምነትን በመጣስ ያደረገው የጥፋት ሙከራ ተቀባይነት የሌለው እና የቡድኑን እኩይ ተልዕኮ በገሃድ ያሳዬ ነው ብለዋል።

ይሄን የጥፋት ተልዕኮ ማውገዝ እና ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ግንባታ መትጋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሰልፉ ተሳታፊዎችም ሕወሓት ትናንት በአማራ ሕዝብ እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ግፍ ለመድገም የሚያደርገውን ሙከራ እንደሚያወግዙም ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያን ገንብተን እንጂ አፍርሰን አናልፍም” ያሉት ሰልፈኞቹ በቀጣይም የጥፋት ተልዕኮን በማውገዝ እና በማክሸፍ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአዲስ አበባ በበጀት አጠቃቀም ከአፍሪካ ቀዳሚ ከተሞች ተርታ መሰለፏ ተገለጸ።
Next articleበአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሠብሥቧል።