
አዲስ አበባ፡ ጥር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል። በጉባኤው ላይ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርትን አቅርበዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸው እንደገለጹት ከተማዋ በገቢ አሠባሠብ እና በጀትን ለዘላቂ ልማት በማዋል ከአፍሪካ ስድስት ከተሞች ቀዳሚ መኾን ችላለች።
በግማሽ ዓመቱ 162 ነጥብ 72 ቢሊዮን ብር ገቢ የተሠበሠበ ሲኾን ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ45 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል ለ195 ሺህ 112 ዜጎች ቋሚ፣ ለ250 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።
150 የሚኾኑ ዓለም አቀፍ ኩነቶችን በማስተናገድ 155 ቢሊዮን ብር ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ እንደኾነም በሪፖርታቸው አስረድተዋል።
በስድስት ወራት ውስጥም 12 ሺህ 232 ፕሮጀክቶች መከናወናቸውን የገለጹት ከንቲባዋ በጤናው ዘርፍም ግዙፍ ሆስፒታሎች እየተገነቡ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ከሚገነቡ ሆስፒታሎች ውስጥ የኮልፌ መንዲዳ እና የንፋስ ስልክ ላፍቶ ዘመናዊ ሆስፒታሎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል። ሆስፒታሎቹም ከ500 በላይ አልጋዎች እንዳሏቸው ነው የጠቆሙት።
ከንቲባዋ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የኾነው እና 511 አልጋዎች የሚይዘው የገላን ትራውማ ሆስፒታል በከተማዋ አንዱ በጤናው ዘርፍ የሚሠራ ሥራ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
በካዛንቺስ የመልሶ ማልማት አካባቢ ዘመናዊ እና ባሕላዊ ስፖርቶች ማዕከል በመጠናቀቅ ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማዋን ወደ ብርሃናማ ምዕራፍ ለማሻገር በተከናወኑ ተግባራት 22 ሺህ የሰላም ሠራዊት መገንባቱን ነው ያብራሩት።
ምክር ቤቱ ሪፖርቱን መርምሮ ካጸደቀ በኋላ፣ የተለያዩ አዋጆችን እና ሹመቶችን ያጸድቃል ተብሎም ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም መሃመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
