የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ሥራ ላይ በበጎ ፈቃደኝነት ለሚሠማሩ ወጣቶች ሥልጠና ሰጠ።

8

 

ባሕር ዳር፡ ጥር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተለያዩ የቅድመ ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ከእነዚህም ተግባራት አንዱ ዜጎች በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን የሥነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት መስጠት በዋነኝነት ይጠቀሳል።

በመኾኑም የቦርዱ የሥነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ከቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ጋር በመተባበር የአዲስ አበባ እና የድሬደዋ ከተማ መሥተዳደሮችን ጨምሮ በክልሎች በመራጮች ትምህርት እና በመረጃ ሥርጭት ዘመቻ ሥራዎች ላይ ለሚሳተፉ 775 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሁለት ቀናት ሥልጠና ሰጥቷል።

የሥራ ክፍሉ ለበጎ ፈቃደኞች ሥልጠና ሲሰጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ሲኾን ከዚህ ቀደም በተለያዩ ቦታዎች ለሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሥልጠናው መሰጠቱ ተገልጿል።

ቦርዱ በሁለት ዙር ያሠለጠናቸውን በጎ ፈቃደኞች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመራጮች ምዝገባ ወቅት የመራጮች ትምህርት እና በምርጫ ቀን የመራጮች መረጃ ሥርጭት ዘመቻ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ በተለያዩ ቦታዎች ለማሠማራት ማቀዱ ተጠቁሟል።

ሠልጣኞቹ በተለይም ዜጎች በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫን እንዲያደርጉ ከማስተማር እንዲሁም ቦርዱ ያለማውን የዲጂታል የመራጮች መመዝገቢያ አማራጭን በሰፊው ከማስተዋወቅ አንጻር ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ይታመናል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article‎አዲሱ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?
Next articleበገበያ ላይ ተወዳዳሪ የሚኾን የሰው ኃይል ለመገንባት የትምህርት ጥራት ድርሻ ከፍተኛ ነው።