
ደብረ ማርቆስ: ጥር 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ለመቀነስ እየሠራ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ አስታውቋል።
ጤናማ የእናትነት ወር በየዓመቱ ከጥር 1 እስከ 30 ባሉ ቀናት የእናቶችን ጤና ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራትን በማከናወን ይከበራል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በሚገኙ ጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎት ሲወስዱ ያገኘናቸው እናቶች በጤና ተቋማት የሚያገኙት አገልግሎት ለሚወለዱ ሕጻናት እና ለእነሱ ጤና መጠበቅ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ነው የገለጹት።
በጤና ጣቢያ ደረጃ የአልትራሳውንድ አገልግሎት ማግኘታቸው ከእንግልት እንደታደጋቸውም ገልጸዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ ሕዳሴ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ የህክምና ባለሙያ የሆኑት ንብረት ውበቴ ለእናቶች ጤና መጠበቅ ቀልጣፋ እና የተሟላ አገልግሎት እየሰጡ መኾኑን ተናግረዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ምክትል ኅላፊ ጌታሁን ላቀው ባለፋት ስድስት ወራት ከ3 ሺህ በላይ ለሚኾኑ እናቶች በጤና ጣቢያ ደረጃ የአልትራሳውንድ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።
የጤና ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ከማዘመን ባለፈ ለእናቶች ተከታታይነት ያለው ግንዛቤ በመፍጠር እና የነፍሰ ጡር ክትትልን በማጠናከር የእናቶችን ሞት መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
በጤና ጣቢያ ደረጃ የእናቶችን ጤና አገልግሎት በማስፋት እና የነፍሰ ጡር እናቶችን ክትትል በማጠናከር ለእናቶች ጤና መጠበቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ስለመኾኑ ከጤና መምሪያው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
