በኮምቦልቻ ከተማ ከ4 ሺህ 300 በላይ የልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ተመረቁ።

6
ደሴ: ጥር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ትዕግሥት ጫኔ በኮምቦልቻ ከተማ ሀሰን አገር ክፍለ ከተማ ነዋሪ ሲኾኑ የአምስት ልጆች እናት ናቸው።
“ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ አልነበረኝም። ልጆቼን ለማሳደግ ተቸግሬ ከቤተሰብ እርዳታ እጠብቅ ነበር” የሚሉት ወይዘሮ ትዕግስት በ2015 በሴፍቲኔት መሳተፍ ከጀመርኩ በኋላ ግን እንጀራ በመጋገር እና በማከፋፈል የተሻለ ገቢ አግኝቻለሁ፤ ኑሮየንም አሻሽያለሁ ብለዋል።
አሁን ላይ ያለማንም እርዳታ ልጆቻቸውን ማስተዳደር መቻላቸውን እና ወደፊትም በተሰማሩበት ዘርፍ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት።
በፍየል እርባታ ዘርፍ የተሰማራው ዳንኤል አሊ እና በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማራው ማዘንጊያ በለጠም በግላቸው ቆጥበው እና በመንግሥት በተሰጣቸው ገንዘብ መነሻነት እየሠሩ ኑሯቸውን ማሻሻላቸውን ተናግረዋል።
በሴፍቲኔት ከታቀፍንበት ጊዜ አንስቶ የቁጠባ እና የሥራ ባሕላችንን አሳድገናል፤ በተሰማራንበት ዘርፍ ውጤታማ በመኾን እና ወደ ምርታማነት በመሸጋገር ለሌሎች የሥራ እድል ለመፍጠር ጠንክረን እየሠራን እንገኛለን ነው ያሉት።
የኮምቦልቻ ከተማ የምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወይዘሮ እታፈራሁ አሰግደው በእለቱ 1 ሺ 268 የቤተሰብ ተጠሪ ያላቸው ከ4 ሺ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች በዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ንዑስ ፕሮግራም ኑሯቸውን እንዲቀይሩ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ማስመረቅ እንደተቻለ አስረድተዋል።
ተመራቂዎች በከተማ ግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአገልግሎት እና በንግድ ዘርፍ ተሰማርተው ሲሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ተጠቃሚዎች ከቆጠቡት በተጨማሪ በተደረገላቸው ክትትል እና ድጋፍ ኑሯቸውን በማሻሻል ከተረጅነት ወደ አምራችነት የተሸጋገሩ ናቸው ብለዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሀመድአሚን የሱፍ በበኩላቸው በከተሞች በርካታ መሥራት እየቻሉ ነገር ግን የመነሻ ገንዘብ ያጡ መኖራቸውን ገልፀው ሃብትን አጣጥሞ መምራት እንደሚያስፈልግ እና መንግሥትም በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሠራ ቆይቷል ነው ያሉት።
ራሳችሁን ችላችሁ ወደ ምርታማነት መግባት ያስፈልጋል፤ ለዚህም ከተማ አሥተዳደሩ ተከታታይ ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል ብለዋል ከንቲባው።
የከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ.ር) የከተማ ሴፍትኔት ፕሮግራም በክልሉ የኮምቦልቻ ከተማን ጨምሮ በ18 ከተሞች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል። ከ195 ሺህ በላይ አባወራዎች እና እማዎራዎች በአካባቢ ልማት፣ በከተማ ግብርና፣ አረንጓዴ ልማት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በተሠሩ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶች ተገኝተዋል ያሉት የቢሮው ኀላፊው በከተማ ሴፍትኔት የታቀፉ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ከድህነት ወጥተው ወደ አምራችነት እንዲሸጋገሩ እና ተመልሰው ወደ ድህነት እንዳይገቡ ተከታታይ ድጋፍ እና ክትትል መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
ዘገቢ:- ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር በጦርነት የተጎዳውን የትምህርት ዘርፍ ለመደገፍ እየሠራ ነው።
Next articleየተመዘበረ ሃብትን በማስመለስ እና የሕግ ተጠያቂነትን በማስፈን ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።