
ሁመራ፡ ጥር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር በጦርነት የተጎዳውን የትምህርት ዘርፍ ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየደገፈ መኾኑን በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳደር አሥታውቋል።
ማኅበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ማኅበራዊ ኀላፊነቶችን እየተወጣ ይገኛል። ከሰሞኑም ከሀገር ውጭ የሚኖሩ የአካባቢውን ተወላጆች እና ማኅበራት በማስተባበር አጋዥ መጽሐፍትን ድጋፍ አድርጓል።
መምህርት የሻለም አየሁን በሰቲት ሁመራ ከተማ አሥተዳደር የኅብረት አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ናቸው።
ምሁራን ማኅበሩ ለትምህርት ቤቱ ያደረገው የአጋዥ መጽሐፍት ድጋፍ ወቅታዊ እና አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በቤተ መጽሐፉ ያሉት የተማሪ መርጃ መጻሕፍት የቆዩ መኾናቸውን የጠቆሙት ርእሰ መምህሯ በድጋፍ የመጡት መጻሕፍት በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የተዘጋጁ በመኾናቸው የተማሪዎችን ውጤታማነት እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።
ምሁራን ማኅበሩ ተማሪዎችን ለመደገፍ እያከናወነው ላለው በጎ ተግባርም ምስጋና አቅርበዋል።
ማኅበሩ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በጦርነት የተጎዳውን የትምህርት ዘርፍ ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየደገፈ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ገብረማርያም መንግሥቴ ናቸው።
አካባቢው በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ በርካታ ትምህርት ቤቶች የወደሙበት መኾኑን አንስተው ከነጻነት በኋላ ባሉት ዓመታት የትምህርቱን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የማኅበሩ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በዚህም ለተማሪዎች የደብተር፣ እስክብሪቶ እና ለሴት ተማሪዎች የንጽሕና መጠበቂያ በየዓመቱ እየደገፈ መኾኑን መምሪያ ኀላፊው ጠቅሰዋል።
በ2017 ዓ.ም ከ950 በላይ መጻሕፍትን ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት። በ2018 ዓ.ም ደግሞ ከ2 ሺህ በላይ አጋዥ መጻሕፍትን ለ25 አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራ ምሁራን ማኅበር ምክትል ሥራ አሥኪያጅ መምህር ደረጀ ማሞ የማኅበሩ ዋና ዓላማ የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ ችግሮች መቅረፍ እንደኾነ ገልጸዋል። በዚህም ትምህርት ላይ ትኩረት አድርገው አየሠሩ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
ትውልድን መቅረጽ አስፈላጊ ጉዳይ ነው ያሉት መምህር ደረጀ ይሄንን ለማድረግ መሠረታዊ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ግድ እንደሚል አንስተዋል።
ከዚህ በፊት ለተማሪዎች እና ለትምህርት ቤቶች ልዩ ልዩ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰው ከሰሞኑም ከሀገር ውጭ የሚኖሩ የአካባቢውን ተወላጆች እና ማኅበራት በማሥተባበር ከ2 ሺህ በላይ አጋዥ መጻሕፍትን ከ870 ሺህ ብር በላይ በኾነ ወጭ ገዝቶ ለዞኑ ትምህርት መምሪያ አስረክቧል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አምሳሉ አሞኘ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
