
ደብረ ብርሃን፡ ጥር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና ቀጣይ የሥራዎች አቅጣጫ ትውውቅ መድረክ ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት እንደገለጹት በቅንጅታዊ አሠራር እና በነዋሪዎች ንቁ ተሳትፎ ከተማዋን የሰላም ቀጣና ማድረግ ተችሏል።
ይህ ስኬት ደብረ ብርሃንን በሀገር አቀፍ ደረጃ የልማት ሞዴል ለማድረግ እንዳስቻለ የጠቀሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ሥራዎች ወደኋላ እንዳይመለሱ ሰላምን በዘላቂነት ማጽናት ወሳኝ መኾኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
“ልማት እንቅፋት አይፈልግም” ያሉት አቶ በድሉ ነዋሪዎች ለሰላም ጠንቅ የኾኑ አካላትን ለሕግ አሳልፈው በመስጠት የዜግነት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የከተማዋ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ዳንኤል እሸቴ አስተማማኝ ሰላም በመኖሩ በርካታ ባለሃብቶች ወደ ከተማዋ እንዲሳቡ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በተከናወኑ የሕግ ማስከበር ሥራዎች የጥፋት ቡድኖችን ሴራ ማክሸፍ መቻሉን እና ታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቁ መደረጉን ኀላፊው በሪፖርታቸው አመልክተዋል።
ነዋሪዎች በብሎክ ተደራጅተው አካባቢያቸውን በመጠበቅ ለጸጥታ መዋቅሩ እውነተኛ አጋዥ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በዕኩይ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ በርካታ ጸጉረ ልውጦችን ለሕግ ማቅረብ መቻሉን የገለጹት አቶ ዳንኤል መጭው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲኾን ከወዲሁ በትኩረት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
“ለጠላት በር አንከፍትም” ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎችም ግጭት ቀስቃሽ አስተሳሰቦችን በበሰለ ውይይት በማርገብ ለልማት እና ለሰላም ዘብ እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።
ሰላምን በማስፈን የከተማዋን የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ሁሉም በቁርጠኝነት እንዲነሳ በመድረኩ ጥሪ ቀርቧል።
ዘጋቢ፦ ስንታየሁ ኃይሉ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
