ሙስና የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚንድ ወንጀል ነው።

4
ሰቆጣ: ጥር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ)
ሙስና በዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ የሚያስቀጣ እንደኾነ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸረ ሙስና ኮንቬንሽን በአዋጅ ቁጥር 544/1999 ላይ አስፍሮት ይገኛል።
ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከሙስና ማዳን መቻሉን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና መከታተያ ክፍል አስታውቋል።
ሙስና የወጣቱን የሥራ ዕድል የሚዘጋ የተወሰኑ ሰዎች ሥልጣንን እና ምቹ ጊዜን ጠብቀው የሚሠሩት የጥፋት ተግባር መኾኑን የተናገረው ወጣት ወንድሙ ገብረ እግዚአብሔር ነው።
ሌላኛው አሥተያየት ሰጭ ደርበው ታረቀኝ ሙስና የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያደቅ፣ “የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚንድ ወንጀል እንደኾነ” ተናግሯል።
እንደ ዋግ ኽምራ ባሉ የመረተ ልማት ችግር ባለበት ዞን ሙስናን መጸየፍ ካልተቻለ ከልማት እና ከእድገት ጋር አብረን መጓዝ አንችልም ነው ያሉት ወጣቶቹ።
ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለመገንባት ሙሰኞችን አስተማሪ ቅጣት በመቅጣት እና በትምህርት ቤቶች ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት መፍትሔ መኾኑን የተናገሩት ደግሞ ደግሞ መምህር ፋንታው ማሞ ናቸው።
ሚዲያዎችም የሚሠሩ ተቋማትን የገንዘብ ቁጥር ከመግለጽ በቂ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባቸው የገለጹት መምህሩ ሕጋዊ የመሰሉ ሙስናዎችን በሕግ አግባብ መመርመር የሚቻልበትን አሠራር መዘርጋት እንደማያስፈልግም ጠቅሰዋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በመንፈቅ ዓመቱ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ከሙስና ማዳኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና መከታተያ ክፍል ኀላፊ መኮንን ከበደ ገልጸዋል።
በሰቆጣ ከተማም 6 ሺህ ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ ያለ አግባብ ከመዘረፍ መታደጉን ነው የገለጹት። ይህም በወቅታዊ ገበያ ሲገመት ከ24 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ጠቅሰዋል።
ሙስናን ለመከላከል የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክረው እንሚቀጥሉ ነው የተናገሩት። ማኅበረሰቡም መሰል ችግሮችን ሲመለከቱ በየወረዳው ላሉ የጸረ ሙስና መኮንኖች በማሳወቅ ሙስናን እንዲከላከሉም አሳስበዋል።
ዘጋቢ ፦ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየወርቅ ምርትን ለማሳደግ በተከናወነ የተቀናጀ ሥራ ውጤት መገኘቱን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next articleየደብረ ብርሃን ከተማ የልማት ሞዴልነቷን ለማስቀጠል ለሰላም ቅድሚያ ሰጥታ እየሠራች ነው።