
አዲስ አበባ: ጥር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ12 የዓለም ሀገራት የማዕድን ዘርፍ ተወካዮች እና የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ተዋናዮች በተገኙበት ዓለም አቀፍ የሲያናይድ ማኔጅመንት ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የውይይት መድረኩ ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሲያናይድ አጠቃቀም በ2025 ዓለም አቀፍ የዕውቅና ምስክር ወረቀት ማግኘቱን ተከትሎ ነው በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ ይህ ጉባኤ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ያለው እና ለማዕድን ሥራ ውጤታማነት የጎላ ሚና ያለው ነው ብለዋል።
የማዕድን ዘርፍ ለሀገር ሁለንተናዊ እና የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወት መኾኑን ጠቅሰዋል። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያለውን እምቅ አቅም በሚገባ ለመጠቀም በርካታ ሥራዎች በትኩረት እየተሠሩ እንዳለም አመላክተዋል።
የማዕድን ልማት ዕድገት የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ባከበረ መልኩ እና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ መከናወን እንዳለበት ያስገነዘቡት ሚኒስትሩ በተለይ የወርቅ ምርትን ለማሳደግ በተከናወነ የተቀናጀ ሥራ እንደ ሃገር ውጤት መገኘቱን አስታውሰዋል።
ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲያናይድ ኬሚካልን በምርት ሂደቱ ላይ በመጠቀም እውቅና ማግኘቱን አድንቀዋል።
ሌሎች የዘርፉ ኩባንያዎች ተሞክሮውን ከሜድሮክ ሊወስዱ እንደሚገባ እና የሲያናይድ ኢንስቲትዩትን እውቅና በማግኘትም በምርት ሂደት ላይ የሲያናይድ ኬሚካልን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
