
ባሕር ዳር: ጥር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች የ”ውከሶንክ” የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል። በአዲስ የተገነባው እና እህት ኩባንያ የኾነውን የ”ጀወከሹ ላምኔት ፈርኒቸር” ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካ ሥራም አስጀምረዋል።
ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሳይበግራቸው የማምረት ሥራቸውን እያከናወኑ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ውስጥ በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የሚገኘው የ”ውከሶንክ” የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንደኾነም ተነስቷል።
ፋብሪካው በ2010 ዓ.ም በ170 ሚሊዮን ብር ወደ ግንባታ መግባቱን የ”ውከሶንክ እና የጀወከሹ” ፋብሪካ ምክትል አሥተባባሪ አበበ ተስፋዬ ገልጸውልናል። ላለፉት ሦስት ዓመት ደግሞ የአካባቢውን ባሕር ዛፋ በመጠቀም ለኮንስትራክሽን አገልግሎት የሚውል ፕላይ ውድ እያመረተ ይገኛል።
ከሰሞኑ ደግሞ እህት ኩባንያ የኾነው የ”ጀወከሹ ላምኔት ፈርኒቸር” ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግንባታውን በማጠናቀ ወደ ሥራ መግባቱን ነው ምክትል አሥተባባሪ የገለጹት። ፋብሪካው የ”ውከሶንክ” የእንጨት ማቀነባበሪያ ፋብሪካን ተረፈ ምርትን በመጠቀም የ”ላምኔቲንግ” ሥራ የሚሠራ ነው።
በሀገሪቱ ከሚገኙ ውስን ፕሮጀክቶች አንዱ እንደኾነም ገልጸዋል። ድርጅቱ በቀጣይ አሁን ካለበት ይበልጥ ለማስፋት ማቀዱንም ተናግረዋል።
ፕለይውድ ማምረት ላይ በሚገኘው ፋብሪካ ለ234 ሠራተኞች በቋሚነት፣ ከ1 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ደግሞ በጊዜያዊነት ለሚሠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት። ለአካባቢው አርሶ አደሮች እና ነጋዴዎችም የገበያ ትስስር መፈጠሩን ነው የገለጹት። ለላምኔቲንግ አገልግሎት የማይውለውን ተረፈ ምርት ደግሞ ማኅበረሰቡ በነጻ እንዲጠቀም ተደርጓል ብለዋል። አሁን ላይ የተጠናቀቀው እህት ኩባንያም ተመሳሳይ የሰው ኃይል የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው የጸጥታ ችግር ግንባታቸውን ያቋረጡ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ሁሉ ችግሩ ሳይበግራቸው በሥራ ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎች መኖራቸውን የደብረ ታቦር ከተማ ከንቲባ ደሴ መኮንን ገልጸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የአካባቢውን የባሕር ዛፍ ጥሬቃ በመጠቀም ፕለይውድ ማምረት ላይ የሚገኘው ፋብሪካ አንዱ መኾኑን ገልጸዋል።
ፋብሪካው ውጤታማ እየኾነ በመምጣቱ ተረፈ ምርቱን ወደ ሌላ ምርት መቀየር የሚችል ፋብሪካ እንዲገነባ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል። ፋብሪካዎቹ ከአካባቢው ባለፈ ለሀገርም የጎላ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በቀጣይ ወደ ሥራ ያልገቡ ሌሎች ባለሃብቶች ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ከተማ አሥተዳደሩም ከተማዋን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ማነቆዎችን ለመፍታት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ፈቃድ የወሰዱም ኾኑ ማልማት የሚፈልጉ አዲስ ባለሃብቶች ገብተው እንዲያለሙም ጥሪ አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስተመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አዲሴ መብራቴ ቢሮው በኢንቨስትመንት ዘርፉ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ባለሃብቶች ወደ ክልሉ ገብተው እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
በተለይ ደግሞ መሠረተ ልማት የማሟላት እና የብድር አቅርቦት የማመቻቸት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። በከተማ አሥተዳደሩ ይታይ የነበረውን የኃይል አቅርቦት መፍታት መቻሉንም ለአብነት አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
