በኮምቦልቻ ከተማ ውስጥ የተገነቡ የልማት ሥራዎች ተመረቁ።

7
ደሴ: ጥር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የምግብ ዋስትና ሴፍቲኔት ጽሕፈት ቤት በከተማዋ የተገነቡ የልማት ሥራዎችን አስመርቋል።
በደረቅ ቆሻሻ፣ በአረንጓዴ ልማት፣ በተፋሰስ ልማት፣ በመሠረተ ልማት እንዲሁም በከተማ ግብርና ከ2014 ዓ.ም እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ በከተማዋ በርካታ ተግባራት መከናወናቸው በዕለቱ ተገልጿል።
ከ12 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም ተነግሯል። ከ2 ሺህ 300 በላይ ነዋሪዎች በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ መኾናቸውም ተገልጿል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ደረጃቸውን የጠበቁ የሕጻናት ማዋያ፣ የወጣቶች ማዕከል እና መሰል ፕሮጀክቶች መሠራታቸው መልካም ነው ብለዋል። በቀጣይም የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ከተሠሩት መካከል በሀሰና ሀገር ክፍለ ከተማ ቁጥር 2 ትምህርት ቤት የመጸዳጃ ቤት እና የአረንጓዴ ልማት፣ በቢራሮ ክፍለ ከተማ 12 ክፍል የማምረቻ እና መሸጫ ሸድ ይገኙበታል ብለዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የምግብ ዋስትና ሴፍቲኔት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እታፈራሁ አሰግደው ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በካፒታል በጀት መሠራታቸውን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶች ሢሠሩ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ የላቀ እንደነበር ተናግረዋል። ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ተግባራት በቀጣይ በትኩረት ይሠራሉም ብለዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወንድወሰን ልሳነወርቅ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደኾነ ገልጸዋል።
በተለይም ለወጣቶች እና እናቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከተማዋን በሁለንተናዊ መንገድ ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑን ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ሰልሀዲን ሰይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የባሕርዳር እፅዋት ቲሹ ካልቸር ማዕከልን ጎበኙ።
Next articleበአማራ ክልል የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ፎረም ምሥረታ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው።