
ደብረ ማርቆስ፡ ጥር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ግለሰቦች አስቀድመው በሚያዋጡት ገንዘብ የቤተሰብ አባሎቻቸው ህመም ሲያጋጥማቸው ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ሕክምና የሚያገኙበት ሥርዓት ነው፡፡
በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ አሚኮ ያገኛቸው ቄስ ተመስገን አወቀ እና አቶ ይበልጣል በዛብህ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡
የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ተጠቃሚ በመኾናቸው ከዚህ በፊት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እና ወጭ በብዙ እንደቀነሰላቸውም ይናገራሉ፡፡
የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይዞላቸው እንደመጣ የሚናገሩት ተጠቃሚዎቹ በመድኃኒት አቅርቦት ረገድ አልፎ አልፎ የሚታየው እጥረት እና ወቅቱን ያልጠበቀ የአገልግሎት ክፍያ መፍትሄ እንደሚያሻው ገልጸዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ጌታሁን ላቀው በ2018 በጀት ዓመት ከ31ሺህ በላይ የሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የጤና መድኅን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም የዕቅዱን 92 በመቶ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት፡፡ በተሠራው ቅንጅታዊ ሥራም በዘርፉ ካለፈው ዓመት የተሻለ መፈጸም እንደተቻለ ነው ምክትል ኀላፊው የገለጹት፡፡
የመድኃኒት እና ተያያዥ የግብዓት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታትም በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ምክትል ኀላፊው የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤትን ሥራንም ለማስጀመር ወደ ተግባር እንደተገባ አስረድተዋል።
የአባላት ክፍያን በተመለከተም ከማኅበረሰቡ የሚነሳውን ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት በ45 ቀናት ውስጥ አስቀድሞ ማጠናቀቅ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
