የአልዋዲ መሥኖ ፕሮጀክት ጉዳይ?

1
ባሕር ዳር፡ ጥር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎የአማራ ክልል መስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ በ2015 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ የአልዋዲ የመስኖ ፕሮጀክት ለመገንባት የዓባይ ኮንስትራክሽን ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር ውል ወስዷል፡፡
ለመኾኑ ፕሮጀክቱ አሁን ምን ላይ ይገኛል?
‎ፕሮጀክቱ የሕዝቡን የዘመናት የመልማት ጥያቄ ለመመለስ እና የግብርና ምርትን በማሳደግ ምጣኔ ሃብታዊ መነቃቃት እንደሚፈጥር ታቅዶ ነው የተጀመረው፡፡
‎አቶ ታፈረ ፈንታየ በጣርማ በር ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ ውኃ በአካባቢያቸው እየፈሰሰ ነገር ግን በመስኖ መጠቀም እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ ችግሩን እንዲፈታ የታሰበው የአልዋዲ መስኖ ፕሮጀክትም በጸጥታ ችግር ምክንያት መጓተቱን ተናግረዋል፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የመዳረሻ መንገድ እና የካምፕ ግንባታም መሠራቱን ገልጸዋል፡፡
‎በዚህ ዓመት ለግድቡ ግንባታ ቁፋሮ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡ አካባቢው ቆላማ እና ዝናብ አጠር ነው፤ የግድቡ መገንባት ለም አፈር ያለበት በመኾኑ ማኅበረሰቡን በእጅጉ እንደሚጠቅም አንስተዋል፡፡ ማኅበረሰቡም ለፕሮጀክቱ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
‎ተቋራጩ ዓባይ ኮንስትርክሽን እንዳለው ፕሮጀክቱ በ2015 ዓ.ም የተጀመረ ነው፡፡ በ25 ወራት ለማጠናቀቅ የታቀደ ቢኾንም ከመነሻው የመንገድ መሠረተ ልማት እና የግንባታ ግብዓት አቅርቦት ችግሮች ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ በስጋት የተቀመጡ ችግሮች ነበሩም ብሏል፡፡
‎በአካባቢው የተከሰተው የጸጥታ ችግርም ፕሮጀክቱ በታቀደለት ጊዜ እንዳይሄድ እና በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለመግባት እንዳስቸገራቸው ተናግረዋል፡፡
‎በአካባቢው በተደራጁ ወጣቶች የሚቀርበው የአሸዋ ምርት ዋጋ የተጋነነ መኾኑ እና ቦታው ወጣ ያለ በመኾኑ የጉልበት ሠራተኞችን አለማግኘት ለሥራው እንቅፋት ኾኗልም ነው ያለው፡፡
‎በአሁኑ ወቅት የመንገድ፣ ካምፕ ግንባታ እና የካናል ቁፋሮን ጨምሮ ፕሮጀክቱ 17 ነጥብ 4 በመቶ ላይ ይገኛልም ብሏል።
ችግሮቹን መፍታት ከተቻለ በ2019 መጨረሻ አካባቢ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ ከ341ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም ይኖረዋል ነው ያለው፡፡
‎የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ችሮታው አስፋው ፕሮጀክቱ ከ270 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለት መጀመሩን አንስተዋል፡፡
በጸጥታው ችግር ቢጓተትም ያለውን አንጻራዊ ሰላም ተጠቅመው ወደሥራ በመግባት በኩል የሥራ ተቋራጩ ውስንነት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
ግድቡ የአካባቢው ማኅበረሰብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ እና ችግር ፈቺ መኾኑ የታመነበት ነው ያሉት መምሪያ ኀላፊው ካለፈው ዓመት መጋቢት ጀምሮ የመዳረሻ መንገድ እና ካምፕ ሥራዎች፣ በቅርቡም የግድብ ግንባታው ቁፋሮ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ተቋራጩ በሙሉ አቅሙ ገብቶ እንዲሠራ እየተወያዩ እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
‎ተቋራጩ ያነሳቸውን ችግሮች ከወረዳው ጋር በመኾን እንደሚፈቱም ነው የተናገሩት፡፡ ግድቡ ሲጠናቀቅ 345 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡
‎በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ እና ድሬይኔጅ ግንባታ ቁጥጥር ዳይሬክተር ጌትነት አያሌው የመስኖ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቁን ገልጸዋል። የመዳረሻ መንገድ ባለመኖሩ እና የነበረውም ለከባድ መኪናዎች አመቺ ባለመኾኑ ተቋራጩ ለመንገድ ሥራው ተጨማሪ ጊዜ ወስዷል ብለዋል።
ቦታው ራቅ ያለ በመኾኑ የኪራይ ማሽነሪዎችን በቅርብ ለማግኘት መቸገሩ ተቋራጩን እንደፈተነውም አንስተዋል።
‎ነባራዊ ሁኔታው ከተቋራጩ አቅም በላይ በመኾኑ የግንባታ ጊዜው መራዘሙን ተናግረዋል፡፡ ውል ለማቋረጥ ሁኔታዎች ባይፈቅዱም ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር በመኾን ተቋራጩ በሙሉ አቅሙ እንዲሠራ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
‎በክልሉ የሚገኙ በርካታ የመስኖ ፕሮጀክቶች በጸጥታ ችግር መጓተታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ ማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግ እና መሥራት እየቻሉ በማይሠሩ ድርጅቶች ላይ የማስጠንቀቂያ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑንም አስረድተዋል።
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበአማራ ክልል የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ጥሩ አፈጻጸም ላይ መኾኑን የክልሉ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።
Next articleየጤና መድኅን ሽፋንን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው።