በአማራ ክልል የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ጥሩ አፈጻጸም ላይ መኾኑን የክልሉ ሥራ እና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

5
ባሕር ዳር፡ ጥር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከሕዝብ የለውጥ ጥያቄ እንቅስቃሴ በኋላ ሀገሪቱን የመለወጥ ኀላፊነትን በ2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሲረከቡ ሀገሪቱ ካለችበት የዘልማድ አሠራር ወጥታ በብዙ የምትቀየርበት ሁኔታን ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ ነው።
ይህን ለውጥ ለመምራት ታዲያ ከአራቱም አቅጣጫ የዓለማችን ሀገራት በፍጥነት እና በአስገራሚ ሁኔታ የተለወጡ ሀገራትን ልምድ መቅሰም የግድ ይል ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አሥተዳደርም ልምዱን በትክክል ቀስመው ወደ ሀገራቸው እንዲያመጡ ሚኒስትሮቻቸውን ወደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ ውስጥ ወደምትገኝ ሲንጋፖር ወደተሰኘች የደሴት ሀገር ልከውም ነበር።
ይህች ሀገር ተፈጥሮ የበደላት ከሚባሉ ቦታዎች ውስጥ ከመመደቧም በተጨማሪ በከፋ ድህነት ውስጥ ወድቃ ምጽዋት የምትማጸንም ነበረች። ይሁን እንጅ ተፈጥሮ ባያድላትም መቀየር እንደምትችል ያመኑ የቁርጥ ቀን የለውጥ ሞተር ልጆቿ ወጥተዋል፤ ወርደዋል።
ይህች ደሴት የሚገርም ለውጥ ለማስመዝገብ የፈጀባት ጊዜ 30 ዓመት ብቻም ነበር። ይህንን ግን በሚገባ ተጠቅማበታለች። ሀገሪቱ ለመቀየር አምሥት ምሰሶዎችን በሚገባ ተግብራለች።
ጠንካራ አመራር መፍጠር፣ በሰው ኀይል ላይ ኢንቨስት ማድረግ፣ ኢንቨስትመንትን ክፍት ማድረግ፣ የሕግ የበላይነት ማስፈን እና የቤት ባለቤትነት ፖሊሲን ተግባራዊ ማድረግ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
ኢትዮጵያም የቀሰመቻቸውን ልምዶች ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለመተግበር እና በአጭር ጊዜ ለውጥ ለማምጣት ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ከአምስቱ ምሰሶዎች ውስጥም በሰው ኀይል ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚለውን ተግባራዊ ለማድረግ የ5 ሚሊዮን የኢትዮ ኮደርስን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የፊት መሪነት በመላው ሀገሪቱ ለመተግበር ጥረት እየተደረገም ይገኛል።
ከዚህ ውስጥ አማራ ክልል የሰው ኀይሉን በማሠልጠን ወደ ማይቀረው የዲጅታል ዓለም ለመቀላቀል ሰፊ ጥረት እያደረገም ይገኛል። በዚህ የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ሂደት ውስጥ ታዲያ ውጤታማ ከኾኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች መካከል የደሴ ከተማ አሥተዳደር አንዱ ነው።
ሀገራዊ ለውጡን በሚገባ ለመቀላቀል እና የተለወጠ ሀገርን ለመፍጠር የሰው ኀይሉን ከቴክኖሎጂ ጋር የማስተዋወቅ እና ሪፎርም የማድረግ ውጤታማ ሥራን የደሴ ከተማ አሥተዳደር መተግበር እንደቻለ የደሴ ከተማ ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ አብዱልሀሚድ ይመር ነግረውናል።
ከተማ አሥተዳደሩ በዚህ ዓመት 4 ሺህ 856 ሰዎችን የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ የሰው ኀይልን ሪፎርም ለማድረግ ጥረት መደረጉን አስረድተዋል። ከ6 ሺህ በላይ የሚኾኑም በሥልጠና ሂደት ላይ እንደሚገኙ ነው የጠቀሱት።
ከተማ አሥተዳደሩ ባለፈው ዓመትም ከተሰጠው 4 ሺህ 500 ሰው በላይ በማሠልጠን የተሻለ የሰው ኀይል ለመፍጠር ጥረት ማድረጉን ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኀላፊ እና የኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ኮሚቴ አባል አማረ ዓለሙ እንዳሉት እንደሀገር ብቁ የሰው ኀይል ለመፍጠር እየተካሄደ ባለው የኢትዮ ኮደርስ ሥራ ጋር ተያይዞ በሦሥት ዓመት ውስጥ 791 ሺህ የሰው ኀይል ለማሠልጠን ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸው ባለፈው ዓመት ከታቀደው ውስጥ 104 በመቶ ማሠልጠን በመቻሉ የሦሥት ዓመቱን ወደ ሁለት ዓመት ማምጣት እንደሚቻል ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ እንደኾነም አስረድተዋል። በዚህ ዓመትም የተሻለ አፈጻጸም መኖሩን ነው የተናገሩት።
አቶ አማረ እንደሚሉት ሀገርን ለመለወጥ እና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር ዜጎች በፍጥነት ወደ ዲጂታላይዜሽን መምጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በሚቀጥሉት ዓመታት ግብርናን ጨምሮ ሁሉም የሥራ ዘርፎች ዲጂታላይዜሽን የመኾን ዕድላቸው ሰፊ በመኾኑ ወደዚህ የለውጥ ባቡር መግባት እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።
ዜጎች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ሥራቸውን መሥራት ካልቻሉ በለውጥ ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊገጥማቸው ስለሚችል ወደ ዲጂታላይዜሽን በፍጥነት ገብቶ እና ሥራዎችን በሚገባ በመምራት ለውጥ ማምጣት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleበእንጅባራ ከተማ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ነው።
Next articleየአልዋዲ መሥኖ ፕሮጀክት ጉዳይ?