
ባሕር ዳር: ጥር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኮሪደር ልማት ለከተሞች እድገት እና ለነዋሪዎች የኑሮ መሻሻል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት። የመሰረተ ልማት አውታሮችን በማዘመን የከተማን ገጽታ ይቀይራል።
ለንግድ፣ ለቱሪዝም እና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶችን ለይቶ በማካተት የትራፊክ መጨናነቅን ይቀንሳል። የትራንስፖርት ፍሰትንም ያቀላጥፋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ እንደተናገሩት በእንጅባራ ከተማ 4 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለማከናወን በእቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው።
በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማትም ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ 1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ማኅበረሰቡም በገንዘብ፣ በጉልበት እና በሀሳብ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ለአብነትም ከ68 በላይ ባለይዞታዎች ቦታቸውን ያለምንም ካሳ በፈቃደኝነት መልቀቃቸውን አንስተዋል። የኮሪደር ልማቱ ከሕዝብ ለሕዝብ የሚሠራ ፕሮጀክት በመኾኑ ማኅበረሰቡ ባለቤት ኾኖ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ የኾኑት አቶ ቦጋለ በቀለ የኮሪደር ልማት መጀመሪያ ሲወራ ግንዛቤው እንዳልነበራቸው ይናገራሉ።
አሁን ላይ በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በጎንደር እና በደሴ ከተሞች የኮሪደር ልማት ተሠርቶ በማየታቸው በእንጅባራ ከተማም እንዲሠራ ጉጉት እንዳደረባቸው ለአሚኮ ተናግረዋል።
አሁን ላይ የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ በመጀመሩ ደስተኛ መኾናቸውን ነው የሚናገሩት። ካላቸው መሬት ላይ ኮሪደር ለሚለማበት 400 ካሬ ሜትር ቦታ ካሳ ሳይጠይቁ ለልማቱ መሥጠታቸውንም ተናግረዋል።
ሌላኛው የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ አቶ አስራት ታደለ የኮሪደር ልማት መጀመሩ ከተማዋ እንድትለማ የሚያደርግ በመኾኑ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ከተማዋ ደምቃ ለትውልድ እንድትተላለፍ የሚያደርግ በመኾኑ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከእንጅባራ ከተማ በተጨማሪ በዳንግላ እና በቻግኒ ከተሞችም ለማስቀጠል የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
