
ባሕር ዳር : ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ በሰሜን ጎጃም ዞን ዳና ማርያም እና ጭምባ ቀበሌዎች ላይ የጽንፈኛውን ርዝራዦች የማጽዳት ግዳጅ እየፈጸሙ የሚገኙ አሃዶችን እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎችን ግዳጅ አፈጻጸም ተመልክተዋል።
በሥፍራው መልዕክት ያስተላለፉት ሌትናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችው ፈጣን እድገት እንቅልፍ የሚነሳቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን የሀገር ተወላጅ በኾኑ ባንዳዎች በኩል ኢትዮጵያን የማተራመስ ፍላጎታቸው ከሽፏል ብለዋል።
የባዕዳን ተላላኪ የኾነው ጽንፈኛው ቡድን በጥምር የጸጥታ ኃይሉ በተወሰደበት እርምጃ ተደምስሷል ነው ያሉት። የተቀሩትም በየገጠር ቀበሌዎች ተበትነው እየተደበቁ የዝርፊያ ተግባር እየፈጸሙ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ሠራዊቱ እግር በእግር አድኖ የማጽዳት ግዳጅ እየፈጸመ መኾኑንም ተናግረዋል። የጸጥታ ኃይሉ በጎጃም ቀጣና እያስመዘገበ ያለውን ስኬታማ ግዳጅ አድንቀዋል፡፡
በዳና ማሪያም እና በጭምባ የተሰማራው ጥምር ጦር የጽንፈኛውን የግድያ፣ የዝርፊያ እና የዕገታ ድርጊቶችን በመግታት ጽንፈኛውን በመምታት የአካባቢውን ሰላም በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ከነክብሯ ለማስቀጠል ፣ የቀደሙ አባቶቻችን ደም እና አጥንታቸውን የከሰከሱበት አደራቸውን ጠብቀን ለቀጣይ ትውልድ ለማስረከብ የምንሠራ የኢትዮጵያ ካርታ ያለበት መለዮ ለባሾች ነን ብለዋል።
መለዮው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚኖሩበት ካርታ ያረፈበት፣ ለክብሩ ሲሉ ብዙ ጓዶቻችን መስዋዕት የከፈሉበት፣ ጠላት ከሩቁ ሲያየው የሚያስፈራ፣ የጠንካራ ሀገር እና የማይበገር ሠራዊት የለበሰው በመኾኑ ልትኮሩ ይገባችኋል ነው ያሉት።
የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ ጽንፈኛውን በመምታት የተወጣቸው ተልዕኮዎች የመፈጸም አቅሙን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ ለመምጣቱ ማረጋገጫ መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
ከምሥራቅ ዕዝ ሚዲያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው መከላከያ ሠራዊትም ኾነ የክልሉ የጸጥታ ኃይል የጀመረውን የማጽዳት ግዳጅ አጠናክሮ በማስቀጠል የሕግ ማስከበር ተልዕኮውን በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
