
ባሕር ዳር: ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ ጉዳት ለሚደርስባቸው ዜጎች መጠባበቂያ የሚኾኑ የእህል ማከማቻ መጋዘኖችን ያዘጋጃል። በሀገሪቱም ሦስት ትላልቅ የእህል ማከማቻ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ናቸው።
ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ በምዕራብ ጎጃም ዞን ማንኩሳ ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘው የፍኖተ ሰላም እህል ማከማቻ ግንባታ ፕሮጀክት አንዱ ነው። የግንባታ ፕሮጀክቱ በ25 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል እህል መያዝ የሚችል ነው።
በ2010 ዓ.ም ተጀምሮ በ2014 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ ወደ ሥራ ቢገባም እስካሁን መዘግየቱ ቅር እንዳሰኛቸው የማንኩሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከ400 በላይ የሚኾኑ ወጣቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ለልማቱ ተብሎ ቢነሱም ፕሮጀክቱ ግን በሚፈለገው ልክ መከናወን አለመቻሉን ገልጸዋል።
ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተስፋ ጥለውበት እንደነበርም ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ እንዲጠናቀቅ የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጠው ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።
ፕሮጀክቱ ለአካባቢው የኅብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ መነቃቃት እንደሚፈጥር ተስፋ በማድረግ የወረዳ አሥተዳደሩ የሚጠበቅበትን ሁሉ ማድረጉን የተናገሩት የጃቢ ጠህናን ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ የቻለ ይርጋ ናቸው።
ፕሮጀክቱ በግንባታ እያለ ከ800 በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሮ እንደነበር ተናግረዋል። ይሁን እንጅ አሁን ላይ በመጓተቱ ምክንያት በነዋሪዎች ላይ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ እያስነሳ መኾኑን ተናግረዋል።
የፍኖተ ሰላም እህል ማከማቻ ግንባታ ፕሮጀክት ተቆጣጣሪ ጳውሎስ ገነቱ ፕሮጀክቱ ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ እየተገነባ መኾኑን ገልጸዋል።
ከተጀመረ አንስቶ እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ የነበረው ተቋራጭ ሥራውን በተገው መንገድ ባለማከናወኑ ፕሮጀክቱ ለሌላ ተቋራጭ መሰጠቱን አንስተዋል።
አሁን ላይ 55 በመቶ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል። ተቋራጩ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ አለመግባት እና የግንባታ ግብዓት አቅርቦት ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የፕሮጀክቱ ተቋራጭ ሥራ አሥኪያጅ ቢኒያም ታደሰ የጸጥታ ሁኔታው የግንባታ ግብዓቶችን ለማቅረብ እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ገልጸዋል። ጣራ ለማልበስ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማቅረብ በሂደት ላይ መኾናቸውንም አንስተዋል።
አሁን ላይ አስቻይ ኹኔታዎች በመኖራቸው በሙሉ አቅም ወደ ሥራ በመግባት በቀጣይ አንድ ዓመት ግንባታውን ለማጠናቀቅ እየሠሩ መኾናቸውን ነው ሥራ አሥኪያጁ የተናገሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
