“የወልቃይት የሕልውና በሕዝብ ውሳኔ እና በሰላም እልባት ማግኘት አለበት” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

17

ባሕር ዳር: ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በፓርላማ ተገኝተው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወሰን እና መፈናቀል ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲኾን ኢትዮጵያውያን በፈለጉት አካባቢ ሠርተው መኖር መብታቸው ስለመኾኑ አስምረውበታል።

ተፈናቃዮች መመለስ እንፈልጋለን ይላሉ፣ በተፈናቀሉባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ይምጡልን እያሉ ነው እና ታዲያ ማነው የያዛቸው የሚለውን ግን ማጤን ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ተፈናቃዮችን አትመለሱም በማለት የሚከለክሉ እንዳሉም ጠቅሰዋል። ገበሬ ዘር ዘርቶ ምርት እንደሚጠብቅ ሁሉ ስደት፣ ሞት እና መፈናቀልን ዘርተው በዚያ ሰበብ እርዳታ የሚፈልጉ አካላትም አሉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

“ተፈናቃዮች ወደቀያቸው የማይመለሱበት ምክንያት ተፈናቃይን መያዣ ያደረገ ፖለቲካ በመኖሩ ነው” ብለዋል። ይህ አካሄድ የሰዎችን ስቃይ የሚያበዛ ስለኾነ መታረም እንዳለበትም አሳስበዋል።

ከየትምውም አካባቢ የተፈናቀሉ ወገኖች በቀያቸው ተመልሰው በሰላም መኖር እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የወልቃይት የይገባኛል ጥያቄ ለረዥም ጊዜ የቆየ ስለመኾኑም ገልጸዋል። የፌዴራል መንግሥት እያለ ያለው ሰዎች በሰላም ይኑሩ፣ ጉዳዩንም ራሳቸው ነዋሪዎች ይወስኑት ነው ብለዋል።

በሕግ አግባብ እና በሕዝበ ውሳኔ እልባት እንዲሰጠውም ጠቁመዋል። “በሕዝብ ህልውና እና መሻት ላይ ማንም ከሚወስን ይልቅ ራሱ ሕዝቡ በሰላም እየኖረ በየት በኩል መሥተዳደር እንደሚገባው መወሰን አለበት እንጅ ማንም ባለሥልጣን “ይሄኛው” ይገባሃል ብሎ መወሰን አይኖርበትም ነው” ያሉት።

ዞኑ ላለፋት ዓመታት ያለበጀት እና ያለድጋፍ የቆዬ ስለመኾኑም ተናግረዋል። ጉዳዩ ሁለት ወንድማማች ሕዝብን በሚያጋጭ መንገድ ሳይኾን በሰላም እንዲፈታ ይፈለጋል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን አይችሏትም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር)
Next articleአካታች ሀገራዊ ምክክርን