
ባሕርዳር፡ ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በተገኙበት መደበኛ ሥብሠባውን እያካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በማብራሪያቸውም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ግንኙነት
ቀይ ባሕርን ስላነሳን ግንኙነት መሻከር የጀመረ የሚመስላቸው እንዳሉ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጸብ የጀመረው የቀይ ባሕርን ከማንሳታችን በፊት ነው ብለዋል። በትግራይ ጦርነት ወቅት የኤርትራ መንግሥት ግፍ ሲፈጽም ተው የሚል ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል ላይ ግፍ መፈጸማቸውን እንዲያቆሙ በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን አንስተዋል። በዚህ የተጀመረው ግጭት የፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈጸም ሕወሓት ሳይጠፋ እንዴት ተፈራረማችሁ ብለው መነሳታቸውን ገልጸዋል።
የትግራይ ሕዝብን ካበሳቆለ ቡድን ጋር ተመልሶ መሥራት ሕዝብን መጥላት እንደኾነም ተናግረዋል። የትግራይ ሕዝብ በኤርትራ ወታደሮች እንዳይዘረፍ ስንጠብቅ ኖረን፤ ሕወሓት ወደ አማራ ክልል ሲገባ ግን አሳፋሪ ተግባር መፈጸሙን ገልጸዋል። ለጊዜያዊ ድል በታሪክ የሚያሳፍር ተግባር መፈጸም እንደማይገባም ተናግረዋል።
ዘላቂ መፍትሔ ላይ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል። ከፋፋይ ሃሳብ ለሀገር እንደማይጠቅምም አንስተዋል። ይህ ደግሞ በዘላቂነት ድል እንደማያመጣ ተናግረዋል።
በጊዜያዊ ጉዳይ ሀገርን የሚጎዳ ሥራ መሥራት እንደማይገባም አመላክተዋል። የእኛ ምርጫ ነገን በሚወስን ጉዳይ ላይ ማተኮር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ተቋም ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጋ እየሠራች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባንዳው ከማቁሰል አያልፍም፣ ዋናው ጠላት ከመጣ ግን መመከት የሚያስችል ተቋም ተገንብቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያን መጉዳት የሚፈልጉ ኀይሎች አሉ፤ ገንዘብ ይከፍላሉ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያን አይችሏትም ነው ያሉት። የእኛ ጉዳያችን ኢትዮጵያ ናት፤ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ጉዳይ ከኾነ ብዙውን በይቅርታ እናልፈዋለን ነው ያሉት።
ለኢትዮጵያ ሲባል ማንም ሰው ለሰላም ዝግጁ መኾን እንደሚገባውም ተናግረዋል። በርካቶች የሰላም አማራጭን እየተቀበሉ እየገቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል።
የብሔራዊ ጥቅም እሳቤ እየተሻሻለ መምጣቱን እና በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ ኀይሎች ትግሉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ መኾኑን ሲረዱ ሰላምን እየመረጡ ነው ብለዋል።
በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት መንግሥት የሚጠበቅበትን እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መሥራት አለባቸው፤ ፖለቲካው ቆይቶ ይመጣል ነው ያሉት። የትግራይ ሕዝብ ሰላም እና ልማት እንደሚፈልግም ተናግረዋል።
ነገር ግን ሥልጡኑ እና ፖለቲካ የሚያውቀው የትግራይ ሕዝብ አሁን ላይ የፖለቲካ መድረክ እንጂ ተዋናይ መኾን እንዳልቻለ ገልጸዋል። የፖለቲካ ተዋናይ ለመኾን ራሱን በአዲስ አስተሳሰብ መቃኘት እንደሚገባውም ተናግረዋል። የፖለቲካ መድረክ ሳይኾን ተዋናይ እንዲኾን መደገፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በትግራይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከአጃቢ ተዋናይነት ወደ መሪ ተዋናይነት መሸጋገር እንደሚገባቸው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ድርቁን እና ዝናቡን አልፎታል፤ ትንንሽ ኮሽታዎች እንደ ወፍ ድምጽ ከማስተናገድ ያለፈ ምንም እንደማይኖርም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
