“የቤት ችግርን ለመቅረፍ እየተሠራ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር)

4

ባሕር ዳር: ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በተገኙበት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

በምላሻቸውም የኑሮ ውድነት ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ መቻሉን ገልጸዋል። ይህም የመጣው በከፍተኛ ሥራ መኾኑን ተናግረዋል። አሁንም በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።

ምግብ እና ቤት ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ትራንስፖርትን ማስተካከል የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አንስተዋል። የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር በተሠራው ሥራ የተገኘው ውጤት ስኬታማ ነው፤ የሚቀረን ግን ገና ብዙ ነው ብለዋል።

የብድር አቅርቦት እና ቁጠባ እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል። ለግል ዘርፉ ብድር እየተመቻቸ መኾኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲኖር የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሠሩ መፈቀዱን ገልጸዋል። ይህም የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር እንደሚያስችል ነው የተናገሩት። የኢትዮጵያ ባንኮች ታላላቅ ባንኮች መኾን እና አቅማቸውን ማደርጀት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።

2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች በስድስት ወራት የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸውም ገልጸዋል። በአካባቢው ያለው የኮሪደር ልማት፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ታላቅ ፕሮጀክቶችን የሥራ እድል እንዲሰፋ አድርገዋል ነው ያሉት። በውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪትም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

አሁንም ተጨማሪ የሥራ እድል መፍጠር እንደሚገባም አንስተዋል። የቤት ችግርን ለመቅረፍ እየተሠራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤቶችም ለመገንባት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

በከተማዋ እና በገጠር ኮሪደር ልማት በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል። በክረምት በጎ ፈቃድም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። ለቤት ሥራ ምቹ የኾኑ ፋብሪካዎች እየተገነቡ መኾናቸውንም አንስተዋል። የቤት መሥሪያ ፋብሪካ እየተገነባ መኾኑንም ተናግረዋል።

በአፍሪካ ፈጣን እድገት እያመጡ ካሉ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ከግንባር ቀደሞቹ መካከል መኾኗን አንስተዋል። የበለጠ እድገት ለማምጣት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል። በጀመርነው ሥራ ከቀጠልን ለልጆቻችን የተሻለ ሀገር እንገነባለን ነው ያሉት።

እያንዳንዱ ዜጋ ለኢትዮጵያ እድገት መሥራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል። በርትተን ከሠራን የሀገራችን እድገት ይረጋገጣል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ብቻ የ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ተኪ ምርቶች ተመርተዋል።
Next article“ባንዳነት ያቆስላል እንጂ አይገድልም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)