
ባሕር ዳር: ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሃሳብ ሰጥተዋል። የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ከ47 እስከ 48 በመቶ ድረስ ነበር ማምረት የሚችሉት ብለዋል።
ዛሬ ላይ በሀገራችን ያሉ ኢንዱስትሪዎች 66 ነጥብ 3 በመቶ የማምረት ምጣኔን ላይ ደርሰዋል ነው ያሉት። ስለዚህ ኢንዱስትሪ ላይ ያለው አፈጻጸም በመልካም ደረጃ ላይ ነው ብለዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች ኃይል አጠቃቀም 16 በመቶ እድገት አሳይቷል ነው ያሉት። እንደ ሀገር 413 ሺህ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዳሉም አንስተዋል።
ታዋቂ ኢንቨስተሮችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ጭምር የሀገሪቱ ኢንዱስትሪ እንዲነቃቃ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል። የቬትናሙ ቶዮ ሶላር ኩባንያ በኢትዮጵያ ሥራ መጀመሩን እንደማሳያ አንስተዋል። በቀጣይ ዓመት ከፀሐይ ብርሃን ኃይል ብቻ 900 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደምናገኝም ታቅዷል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት እና በዚህ ዓመት ብቻ ያለውን የኢንዱስትሪው ኤክስፖርት ምጣኔ በእጥፍ አድጓል ብለዋል። ኢንዱስትሪዎች ተኪ ምርትን እንዲያመርቱ በማድረግ በኩልም የተሠራው ተግባር የሚናቅ አይደለም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ታምርት በሚለው ንቅናቄ ብቻ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ገቢ እናደርግበት የነበረውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል ነው ያሉት።
የማዕድን ገቢ ላይም በዚህ ስድስት ወር 30 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ነው ያሉት። ይህን ዓይነቱን ዕድገት እያደነቅን ለበለጠ ሥራ ግን መትጋት ጤናማ እሳቤ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
የተሠራውን እየነቀፍን ሳይኾን የጎደለውን በትብብር እየሞላን ከሄድን የበለጠ ለውጥ እናመጣለን ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
