“ኢትዮጵያ ለሕዳሴ ግድብ አንድ ብር እርዳታ አልወሰደችም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

4

ባሕር ዳር: ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በተገኙበት መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ( ዶ.ር) ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

በምላሻቸውም ኢትዮጵያ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል። በስድስት ወራት 709 ቢሊዮን ብር መሰብሰቧን ገልጸዋል።

በሰባት ወራት ደግሞ 810 እስከ 815 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት ነው የተናገሩት። በሰባት ወራት ይሄን ከሰበሰብን 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ዕቅድ ያንሳል ብለናል ነው ያሉት። ከዚህ በላይ መጨመር አለብን ብለን እየሠራን ነው ብለዋል።

2 ነጥብ 6 ሚሊዮን የንግድ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ መቁጠሩን ነው የተናገሩት። ይህም የገንዘብ ስወራ እንዳይኖር ማድረጉን ገልጸዋል። ገቢው እና ወጪን ማመጣጠን እንደሚገባ ተናግረዋል። ወጪ ላይ ተጨማሪ ሥራ ቢያስፈልግም የተሻለ ሥራ እንዳለ ገልጸዋል።

እንደ ሀገር የተደረገው ለውጥ ክብር ይሰጠው ከኾነ ክብር የሚያሰጣው ዕዳ ቅነሳ ላይ የተሠራው ሥራ መኾኑን ተናግረዋል። ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ በኮመርሻል ሎን አንድ ዶላር አለመበደሯን ገልጸዋል። ይህን በማድረጓ ስኬታማ መኾኗን ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ያለ ምንም ብድር ሕዳሴን ማሳካት መቻሏንም ገልጸዋል። በሕዳሴ ግድብ ላይ አንድም ብድር፣ አንድ ብር እርዳታ አልወሰደችም፤ በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ቁርጠኝነት የተከወነ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ይበቃል ሳትል በአፍሪካ ሦስተኛ የኾነው ኮይሻን እየገነባች መኾኗን አንስተዋል። ከአፍሪካ አንደኛው ኤርፖርት ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል። የማዳበሪያ ፋብሪካም በኢትዮጵያ እየተሠራ ነው፤ የጋዝ ፋብሪካም እየተሠራ ነው ብለዋል።

በፕሮጀክት አፈጻጸም አፍሪካ ከኢትዮጵያ ትማራለች ነው ያሉት። ፕሮጀክት ተጀምሮ እንዳይቆም ቀን እና ሌሊት እየሠራች መኾኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ምርት ገቢ ማግኘቷን ተናግረዋል። ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር መምጣቱን ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትን እና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በትኩረት መሥራቷን ተናግረዋል። የዋጋ ግሽበትን የሚያባብሰው የፍላጎት እና የአቅርቦት መራራቅ ነው ብለዋል። ይሄን ለመፍታት ምርታማነትን የመጨመር ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። መንግሥት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ደመወዝ መጨመሩንም አንስተዋል።

እኛ በችግር ውስጥ እያለፍን ልጆቻችን ከችግር እንዲወጡ ማድረግ አለብን ነው ያሉት። በጡረታ ለሚገኙ ወገኖችም ተደጋጋሚ ጭማሪ መደረጉን አንስተዋል። መንግሥት ነዳጅ እና ማዳበሪያ ላይ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። የቅዳሜ እና እሁድ ገበያን በማስፋፋት የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የግብርናው ዘርፍ መጠነ ሰፊ ለውጥ አምጥቷል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleበኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ብቻ የ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ተኪ ምርቶች ተመርተዋል።