
ባሕር ዳር: ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያዎችን እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ለዕድገት መሠረት የሚኾን የኢኮኖሚ ሪፎርም ሥራ መተግበሩን ገልጸዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራትን ማረቅ፣ ግብርና መር ብዝኀ ዘርፍ ዕድገት እና የሀገርን የብድር ቀንበር ማቅለል ዋና ዋና የሪፎርሙ ትኩረት ስለመኾናቸውም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውጤታማ የሚባል የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብም ተችሏል ብለዋል። የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አሁን ላይ ያለው እዳ ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዳይሻገር የሚያስችል፣ ኢትዮጵያን ማሳደግ ብቻ ሳይኾን የአፍሪካ ተምሳሌትም ማድረግ የሚችል ነው ብለዋል።
የታለመው ዕድገት የሚሳካው ቴክኖሎጂን ተጠቅመን ሥንሠራ ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፎርሙ ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ ትኩረት ስለመስጠቱም አብራርተዋል።
ወጣቶችን ለነገ ኢኮኖሚያዊ ውድድር ማዘጋጀት ያስፈልጋል፤ ኢትዮጵያም በተለይም በቴክኖሎጅው ዘርፍ ትውልድ ላይ አበክራ እየሠራች ነው ብለዋል። ከአፍሪካ ቀድመን የኤ አይ ኢንስቲትዩት አቋቁመናል ነው ያሉት።
በዓለም ላይ አንድ ብቻ የኤአይ ዩኒቨርሲቲ እንዳለ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዩኒቨርሲቲ እየገነባች ነው፤ ከስድስት ወራት በኋላም ሥራ ይጀምራል ብለዋል።
በአምስት ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና 3 ሚሊዮን ዜጎች ሥልጠናውን ማጠናቀቃቸውን እና ቀሪዎች ደግሞ እየሠለጠኑ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
በዓለም ላይ 10 ፈጣን አዳጊ ሀገራት ተመዝግበዋል፤ አምስቱ አፍሪካ ውስጥ ናቸው ብለዋል።
በዚህ ዓመት 9 ነጥብ 2 እድገት እናመጣለን ብለን አቅደን ነበር፤ ከስድስት ወራት የአፈጻጸም ውጤት በመነሳትም ከዚያ በላይ ማደግ ስለሚቻል ወደ 10 ነጥብ 2 አሻሽለናል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
