በአማራ ክልል የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ተቋማዊ ብቃት ያላቸው እንዲኾኑ እየተሠራ ነው።

1

ባሕር ዳር: ጥር 26/2018 (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉን ፍርድ ቤቶች የ2018 የበጀት ዓመት የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ዓለም አንተ አግደው፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎች እና የአሥተደደር ሠራተኞች በተገኙበት ገምግሟል፡፡

የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ፍሬው ታደሰ የክልሉ ፍርድ ቤቶች ተቋማዊ ብቃት ያላቸው፣ የዳኝነት ነፃነት እና ተጠያቂነት የሠፈነባቸው፣ ውጤታማ የኾኑ፣ የሕዝብ አመኔታን ያተረፉ እና ተምሳሌት የኾኑ ፍርድ ቤቶች እውን ማድረግ የሚል ርዕይ ተቀርጾ ሁለንተናዊ ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር እና በማስከበር ፍርድ ቤቶች የመጨረሻ የመብት ማስከበሪያ ተቋማት መኾናቸውን ለማረጋገጥ መጠነ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን አብራርተዋል፡፡

ውሳኔ የሚያገኙ መዛግብት ብዛት በመጨመር፣ የማጥራት አቅምን ለማሳደግ እና የመጨናነቅ ምጣኔን ለመቀነስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ከመቼውን ጊዜ የተሻለ የሥራ አፈጻጸም ሊመዘገብ ችሏል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የክልሉ ፍርድ ቤቶች የሥራ አፈጻጸም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ መኾኑን ገልጸዋል። የሚወሰኑ መዛግብትን መጠን እና የዳኝነት አገልግሎት ጥራትን በማሻሻል ረገድ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች የተመዘገቡ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

የሥራ አፈጻጸም የግምገማ መድረኩን የመሩት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ ፍርድ ቤቶች የግማሽ ዓመት ሥራ አፈጻጸም አመርቂ ውጤት የታየበት መኾኑን አስረድተዋል። በተሰሩ ተከታታይነት ያላቸው የለውጥ ሥራዎች የክልሉ ፍርድ ቤቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸው እምነት እና ቅቡልነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል። በቀጣይም ፍርድ ቤቶች ነጻ እና ገለልተኛ ኾነው ሕግ የመተርጎም ኀላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ የሚያስችሉ ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡

የዳኝነት አገልግሎት ጥራትን በተመለከተ አሁንም መሻሻል የሚሹ በርካታ ጉዳዮች ያሉ ቢኾንም ተጨባጭ ለውጥ እየታዬ መምጣቱን ገልጸዋል። የዳኞች የእርስ በእርስ የሕግ ውይይት በተዘረጋው መምሪያ መሰረት ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው መኾኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የዳኝነት አገልግሎት በኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ እንዲደገፍም ተደርጓል ነው ያሉት። የዜጎችን አማራጭ ፍትሕ ማግኛ መንገዶችን ለማስፋት በማሰብ የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና እውቅና ለመስጠት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።

የፍትሕ አገገልግሎት በአንዱ ተቋም ተጀምሮ እዚያው የሚጠናቀቅ ባለመኾኑ የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት ተቀናጅተው ሊሠሩ የሚገባ መኾኑን ጠቅሰዋል። የትብብር መድረክ አባል ተቋማት የዘርፉን ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማሳካት ሊረባረቡ ይገባል ብለዋል፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓትን ለመገንባት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል።
Next articleኢትዮጵያ በዓለም ሁለተኛውን የኤ አይ ዩኒቨርሲቲ እየገነባች ነው።