ዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓትን ለመገንባት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል።

5

ባሕር ዳር: ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በተገኙበት መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።

የምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) ጥያቄዎችን እና አስተያየት እያቀረቡ ነው።

ኢትዮጵያ የማርበርግ በሽታን የተቆጣጠርቸበት መንገድ የሚደነቅ መኾኑን ተናግረዋል። የጤና ግብዓቶችን፣ መሣሪያቸውን እና መሠረተ ልማቶችን በማሟላት በኩል ግን አሁንም ክፍተት እንዳለ አንስተዋል።

የመድኃኒት ውድነትን ለመፍታት እና በሀገር ውስጥ ለማሟላት ምን እየተሠራ እንደኾነ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

መንግሥት ምርጫው ውጤታማ እንዲኾን ሚዲያዎች ሁሉንም በእኩል እንዲያገለግሉ ማድረግ ይገባዋል ነው ያሉት። የፓርቲ እና የመንግሥትን መስመር መለየት እና የሚዲያዎችን ነጻነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት እንደሚገባም ገልጸዋል።

መንግሥት የኢኮኖሚ ስብራትን ለመጠገን እየሠራው ያለው ሥራ የሚደነቅ መኾኑን ገልጸዋል። መንግሥት ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ማጠናቀቅ መቻሉንም አንስተዋል። ሀገር የምትገነባው በመደማመጥ እና በአንድነት ነው ብለዋል።

በከተሞች ላይ እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማት እና ሌሎች ልማቶች የሚደነቁ መኾናቸውን ገልጸዋል። መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር በነዳጅ ላይ እያደረገው ያለው ድጎማ የሚመሰገን ነው፤ ነገር ግን አሁንም በየወሩ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እየተካሄደ ነው፤ የነዳጅ ሥርጭት ችግርም አልተፈታም፤ አሁንም በየማደያዎች ረጃጅም ሰልፎችን ማየት የተለመደ ነው፤ ይህ እንዲፈታ ምን እየተሠራ እንደኾነም ጠይቀዋል።

ምርጫው ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲኾን መንግሥት የሚጠበቅበትን ማድረግ እንደሚገባው ተናግረዋል። መንግሥት ምርጫው ፍትሐዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና ተዓማኒ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ምን ዓይነት ዝግጅት እያደረገ እንደኾነም ጠይቀዋል።

ዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት የውይይት ባሕልን ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል። ለዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባም ገልጸዋል። ዜጎች በሰላም እጦት እየተሰቃዩ፣ እየታገቱ እና በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ እየተደረጉ መኾናቸውንም አንስተዋል።

የፍትሕ ዘርፉ ያለበትን ችግር መፍታት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleብሔራዊ ጥቅም መንግሥታት ሲቀያየሩ የማይቀያየር የሀገር ጥቅም ነው።
Next articleበአማራ ክልል የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ተቋማዊ ብቃት ያላቸው እንዲኾኑ እየተሠራ ነው።