ብሔራዊ ጥቅም መንግሥታት ሲቀያየሩ የማይቀያየር የሀገር ጥቅም ነው።

3

ባሕር ዳር፡ ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት መደበኛ ስብሰባውን ማካሄድ ጀምሯል።

የምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ነው።

የምክር ቤት አባላት መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየሠራ ያለው ሥራ የሚመሰገን መኾኑን ተናግረዋል። ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የፕሪቶሪያ ስምምነት ትልቅ አስተዋጽኦ ቢያደርግም የሕወሃት ክፋይ ቡድን ግን ለጦርነት እየተነሳ መኾኑን ገልጸዋል። መንግሥት በዚህ ጉዳይ ምን ዓይነት ሥራዎች እየሠራ እንደኾነም ጠይቀዋል።

የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት እና የዋጋ ግሽበት ዜጎችን እየፈተነ መኾኑን አንስተዋል። መንግሥት ይህን ችግር ለመፍታት ምን እየሠራ እንደኾነም ማብራሪያ ጠይቀዋል።

የመንግሥት ሠራተኞችን እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን ታሳቢ ያደረገ የቤቶች ግንባታ ማካሄድ እንደሚገባም ተናግረዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ያለው ግጭት ኢኮኖሚው እንዲዳከም እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

የምክር ቤት አባላት ሰላም ካልተረጋገጠ ዘላቂ ልማትን ማምጣት እንደማይቻል ነው የገለጹት። የፖለቲካ ልዩነት እንዳለ ኾኖ በሀገር ብሔራዊ ጥቅም ሁሉም በአንድነት ይቆማሉ ነው ያሉት። ብሔራዊ ጥቅም መንግሥታት ሲቀያየሩ የማይቀያየር የሀገር ጥቅም ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግን በብሔራዊ ጥቅም የሚደራደሩ ቡድኖች እና ግለሰቦች እየተፈጠሩ ነው፤ መንግሥት ይሄን ለማስተካከል ምን እየተሠራ እንደኾነ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲ ለማሳደግ እየተሠራ ያለው ሥራ የሚደነቅ መኾኑንም ገልጸዋል። ግጭትን እና ድህነትን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባም አባላቱ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርብ የመስኖ ግድብ ለግንባታ የወጣውን ገንዘብ መቼ ሠርቶ ይመልሰው ይኾን?
Next articleዘላቂ የፖለቲካ ሥርዓትን ለመገንባት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል።