ርብ የመስኖ ግድብ ለግንባታ የወጣውን ገንዘብ መቼ ሠርቶ ይመልሰው ይኾን?

3

ባሕር ዳር: ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የርብ መስኖ ልማት ግድብ የመሠረት ድንጋዩ ከተጣለ 18 ዓመታትን አስቆጥሯል። አንድ ሁለት እያለ ከወጣትነት ዕድሜው ላይ ደርሷል።

በአራት የግንባታ ተቋራጮች እጅ ላይም አልፏል፤ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ፈሰስ ተደርጎበታል። እንዲህም ኾኖ አሁን ያለበት ቁመና ያላለቁ ፕሮጀክቶች ምሳሌ ይመስላል።

የግድቡ ካናሎቹ ተገንብተው ባለመጠናቀቃቸው ከአርሶ አደሮቹ ማሣ ላይ በቅጡ አልደረሱም። ዕድለ ቢሱ ርብ አሁንም በክልሉ የጸጥታ ችግር ምክንያት የካናል ግንባታ ሥራው ያዝ ለቀቅ ኾኗል።

ፕሮጀክቱ ሲጀመር 20 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚያለማ፣ ከ28 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የልማቱ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። የአሁናዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግን የሚያለማው የመሬት መጠን ቀደም ሲል ከተጠቀሰው በግማሽ ዝቅ ብሏል።

ይሄም ቢኾን እየለማ አይደለም ያሉት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ እና የመስኖ ዘርፍ አስተባባሪው አየልኝ መኳንንት ናቸው።

አቶ አየልኝ መኳንንት እንደሚሉት የካናል ሥራዎች ለሁለት ተቋራጮች የተሠጠ ቢኾንም በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ሥራቸውን አልጨረሱም።

የዓባይ ኮንስራክሽን ከ3 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ውል ወስዶ የታችኛውን ርብ የካናል ግንባታዎች እየሠራ ያለ ተቋራጭ ድርጅት ነው።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ምክር ተስፋሁን በክልሉ የጸጥታ ችግር ለሥራቸው እንቅፋት ቢኾንም የሕይዎት መሰዋዕትነትም ከፍለን እየሠራን እንገኛለን ብለዋል። አንድ የድርጅታቸው ከፍተኛ ባለሙያ በጸጥታው ችግር ምክንያት በሥራ ላይ እንዳለ ሕይዎቱ ማለፉንም አስረድተዋል።

የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ደግሞ ከ7 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የሚለማበትን የላይኛውን ርብ የካናል ሥራዎች ለማከናወን ውል ቢወስድም 43 በመቶ ላይ እንደደረሰ ግንባታውን አቋርጧል።

የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ሥራ አሥፈጻሚ ኤርሚያስ እምሬ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እና የካሳ ግምት አለመከፈል ግንባታውን ባቀዱት ልክ ለመተግበር እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ተቋራጮች የጠቀሷቸው ምክንያቶች ዕውነትነት ቢኖራቸውም የተቋራጮች የመፈጸም አቅም ውስንነትም ጎልቶ ይታያል ብለዋል የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ እና የመስኖ ዘርፍ አስተባባሪው አየልኝ መኳንንት።

ሌላው ለርብ የመስኖ ልማት የካናል ሥራዎች መጓተት ትልቁ ችግር የካሳ ክፍያ መኾኑን የክልሉ መሬት ቢሮ መረጃ ያሳያል። በክልሉ መሬት ቢሮ የካሳ እና መልሶ ማቋቋም ዳይሬቶሬት ዳይሬክተር ምስጋናው አባተ እንደሚሉት አዲሱ የመሬት ካሳ አዋጅ 1336/2016 ከመጽደቁ በፊት በፌዴራል መንግሥት መከፈል የነበረበት 350 ሚሊዮን ብር ገደማ ለባለይዞታዎች አልተከፈለም። በጥቅሉ የ418 ባለይዞታዎች የካሳ ክፍያ ባልተፈጸመበት ሁኔታ የርብ ግድብ የካናል ግንባታ ሥራዎች ይጠናቀቃል ብሎ መጠበቅ ከባድ ነው።

በፌዴራል መንግሥት የርብ የመስኖ ልማት ግድብን በባለቤትነት የሚቆጣጠረው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ነው። ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በካሳ ክፍያው ዙሪያ መረጃ ለማግኘት የሚኒስቴሩን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር በተደጋጋሚ ለማናገር ብንሞክርም መረጃ ለመስጠት ጊዜ እንደሌላቸው በመግለጽ ፈቃደኛ አልኾኑም። ፈቃደኛ ሲኾኑ ሃሳባቸውን የምናካትት ይኾናል።

ዘጋቢ:- ደመወዝ የቆዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየማስተማሪያ ሪፈራል ሆስፒታሉን ሥራ ለማሥጀመር እየተሠራ ነው።
Next articleብሔራዊ ጥቅም መንግሥታት ሲቀያየሩ የማይቀያየር የሀገር ጥቅም ነው።