
ባሕርዳር፡ ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ የማስተማሪያ ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታን ጎብኝተዋል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ ሪፈራል ሆስፒታል በ2010 ዓ.ም የግንባታ ሥራው ቢጀመርም በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠረው የጸጥታ እና ሌሎች ችግሮች ምክንያት ሲጓተት መቆየቱን የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሰለሞን አበጋዝ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ በ2017 ዓ.ም የሆስፒታሉ ግንባታ በአዲስ ውል ተሰጥቶ በተሻለ መንገድ እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።
አሁን የተጀመሩትን ግንባታዎች ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅም ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ውል ተወስዶበታል። ዶክተር ሰለሞን አበጋዝ እንደገለጹት የሆስፒታሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከ800 በላይ አልጋዎች ይኖሩታል።
ሁሉንም ዓይነት ሕክምናዎችምን መስጠት የሚችል ሆስፒታል መኾኑንም ነው የገለጹት። ሆስፒታሉ በሚቀጥለው ዓመትም በከፊል ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይታሰባል።
ይህም ማኅበረሰቡ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተጉዞ ለመታከም የሚያወጣውን ጊዜ፣ ጉልበት እና ወጭ የሚያስቀር ነው።
በደብረ ታቦር ሆስፒታል የሚፈጠረውን መጨናነቅም ይቀርፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ከደቡብ ጎንደር ዞን ሕዝብ ባለፈ በአጎራባች ዞኖች እና ክልሎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችልም ነው ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
