የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓል በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር እየተከበረ ነው።

4
ባሕር ዳር: ጥር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በበዓሉ መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን ደብረ ታቦር ከተማ በአጼ ሰይፈ አርእድ ዘመነ መንግሥት መቆርቆሯን አስታውሰው በአራቱም አቅጣጫ የሚያዋስናትን ከባቢ ለመቃኘት ምቹ መኾኗን ገልጸዋል።
ደብረ ታቦርን ጥንታዊነት እና ታሪካዊነት ብቻም ሳይኾን በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መዲና ኾና ማገልገሏን ጠቅሰዋል። ለሀገረ መንግሥት ምሥረታ አስተዋጽኦ እንደነበራትም አንስተዋል።
አካባቢው ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ሃብቶችን የያዘ የጥበብ ምድር ነው። መሠረተ ልማት የተሟላለት እና ለባሕር ዳር በቅርበት የሚገኝ ነው ብለዋል።
ሴባስቶፖል መድፍን ለመሥራት የተጀመረበት እና የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅነቱንም ጠቁመዋል። በከተማ አሥተዳደሩ የአጼ ቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት እና የሴባስቶፖል ኢንዱስትሪ መንደር፣ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የትውልድ ሀገር የሚገኝበት ከተማ መኾኑን ጠቅሰው የበርካታ ባሕላዊ እሴቶች እና ታሪካዊ ቦታዎች ባለቤት መኾኑን ተናግረዋል።
ጥር 25 ቀን የሚከበረው የንግሥና እና የፈረስ በዓል ጨዋታ እና ትርኢት በአጅባር ሜዳ የሚታዩ መኾናቸውም ከተማዋን ልዩ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።
የፈረስ ጉግሥ ጨዋታ ከተጀመረ ብዙ ዓመታትን እንዳስቆጠረ የገለጹት ከንቲባ ደሴ መኮንን ከድሮ ጀምሮም ተወዳጅነቱን አንስተዋል። የፈረስ ጉግሥ ጨዋታ በአንድ በኩል የሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስን ገድል የመዘከር ሃይማኖታዊ ገጽታ እንዳለው እና በሌላ በኩል ደግሞ ቀደምት አባቶቻችን ሀገርን ለመጠበቅ ሲዘምቱ የሚጠቀሙበትን የፈረስ ግልቢያ ለመዘከር የሚከበር መኾኑን ገልጸዋል።
ጨዋታው በተደራጁ ፈረሰኞች የሚደረግ ውድድር እና ትርኢት ሲኾን ተመልካቾች እየደገፉ እና እያደነቁ የሚመለከቱት መኾኑንም ጠቅሰዋል።
በዓሉ እምነት፣ ባሕል እና ማንነት ተጣምረው በታረካዊቷ ደብረ ታቦር አጅባር ሜዳ የሚከበር በመኾኑ ልዩ እንደኾነም ተናግረዋል።
ደብረ ታቦር ከተማ በየዓመቱ ጥር 25 ቀን የምትደምቅበት በመኾኑም በሀገር ውስጥም ኾነ በውጪ የሚኖሩ ወገኖች በዓሉን እንዲያከብሩ ጥሪ አድርገዋል።
ለበዓሉ የተገኙ እንግዶችም የደብረ ታቦር እና አካባቢውን ባሕላዊ እሴቶች እና የታሪክ ሃብቶች እንዲጎበኙ ጋብዘዋል። ከተማዋን ለሚያለሙ ባለሃብቶች ምቹ መኾኗን እና የከተማ አሥተዳደሩም አስፈላጊው ሁሉ እንደሚደግፍ ገልጸዋል።
በዓሉ በአማረ እና በደመቀ ኹኔታ እንዲከበር አስተዋጽኦ ላበረከቱት ሁሉ አመስግነዋል። በዓሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ለሚደረገው ጥረትም አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ሀገራዊ ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ አካላት ሚና የጎላ ነው” የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሠብሣቢ ሜላተወርቅ ኀይሉ
Next articleበማይካድራ ከተማ አሥተዳደር ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።