
አዲስ አበባ: ጥር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
መልካም አሥተዳደርን ለማጎልበት እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደትን ለማጠናከር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሠብሣቢ ሜላተወርቅ ኀይሉ ተናግረዋል።
7ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድም ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የተናገሩት ሠብሣቢዋ በተለይም ምርጫ ቦርዱ አዋጅ 11/62ን
በማሻሻል እና መመሪያዎችንም በማስተካከል ሥራዎችን እየሠራ እንዳለ አመላክተዋል።
ዜጎች በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ እንዲያደርጉ ለመራጮች ትምህርት መስጠት በምርጫው የሚሳተፉ የሲቪል ድርጅቶች አስተባባሪዎች ታዛቢዎችን እና የምርጫ አስፈፃሚዎችን የመመልመል ብሎም አስፈላጊውን ግብዓት እና ሥልጠና የማሟላት ሥራዎች እንደተሠሩም ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሠብሣቢ ሜላተወርቅ ኀይሉ ሀገራዊ ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ አካላት የጎላ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።
የቦርድ ሠብሣቢዋ የጸጥታ አካላት የክልል መንግሥታት እና የከተማ አሥተዳደሮች በየጊዜው ተለዋዋጭ ለኾነው የሰላም ሁኔታ ትኩረት በመስጠት እና በቅንጂት በመሥራት ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ብሎም ውጤታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
በጸጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ መካሄዱም ሀገራዊ ምርጫውን ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በማድረግ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ስለመኾኑ ጠቁመዋል።
በመድረኩ የሁሉም ክልሎች ፕሬዝዳንቶች፣ የከተማ አሥተዳደር ከንቲባዎች እና ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ታዳሚ ኾነዋል። መድረኩም ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል።
ዘጋቢ፦ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
