ኀብረት ሥራ ማኅበራት ምርትን በብዛት እና በጥራት በማቅረብ በገበያው ትርጉም ያለው ልዩነት እየፈጠሩ ነው።

6
አዲስ አበባ: ጥር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ​በኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ለ12ኛ ጊዜ፣ በአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ደግሞ ለ5ኛ ጊዜ የተዘጋጀው የኅብረት ሥራ አውደ ርዕይ ባዛር እና ሲምፖዚየም በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መካሄድ ጀምሯል።
የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽታዬ ሙሐመድ በከተማዋ በኀብረት ሥራ ማኅበራት በተከናወነ ሪፎርም የገጠር ምርትን ከከተማ ግብይት፤ አምራችን ከሸማች ጋር በቀጥታ በማገናኘት አካታች ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ማኅበራዊ ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌትነት ታደሰ ኀብረት ሥራ ማኅበራት ከባሕላዊ አሠራር ወጥተው የአዲሱ ትውልድ ኀብረት ሥራ መገለጫ የኾኑ ገበያ ተኮር፣ ተወዳዳሪ፣ ተጠያቂ እና ዘላቂ የቢዝነስ ተቋማት እንዲኾኑ ትራንስፎርሜሽን እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በትራንስፎርሜሽኑ ኀብረት ሥራ ማኅበራት ከምርት እስከ ግብይት ባለው ሁሉን አቀፍ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ምርትን በብዛት እና በጥራት በማቅረብ በገበያው ትርጉም ያለው ልዩነት እየፈጠሩ ነው ብለዋል።
በዕለቱ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ የኀብረት ሥራ ማኅበራት በግብርና ግብዓት አቅርቦት እንዲሁም በከተሞች የምርት አቅርቦት እና ግብይት፤ በቅዳሜ እና እሑድ ገበያዎች በንቃት በመሳተፍ፤ የገበያ ዋጋን በማረጋጋት የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
እሴት በመጨመር ሀገራዊ ሚናቸው ከፍ እንዲል መንግሥት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። በዘንድሮው አውደ ርዕይ እና ባዛር ከ360 በላይ ኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚሳተፉ ሲኾን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የቀጥታ ግብይት እና የገበያ ትስስር ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኅብረት ሥራ አውደ ርዕይ ባዛር እና ሲምፖዚየም እስከ ጥር 30/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡
ዘጋቢ፦ኢብራሂም መሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleማኅበረሰቡ ከትራፊክ አደጋዎች ራሱን ለመጠበቅ የትራፊክ ሕጎችን ሊያከብር ይገባል።
Next articleበዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።