
ደብረማርቆስ: ጥር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ባለፉት ስድስት ወራት ዘጠኝ የትራፊክ አደጋዎች ተከስተው በሰው ሕይዎት እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችል የትራፊክ ሳምንት አክብሯል። የከተማ አሥተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ የመንገድ እና ትራፊክ ደኅንነት ዋና ክፍል ኀላፊ ኮማንደር ነገሰ አባተ እንደገለጹት የትራፊክ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየኾነ መጥቷል።
ባለፉት ስድስት ወራት የተከሰቱት የትራፊክ አደጋዎችም ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር፣ ለእግረኛ ቅድሚያ ባለመስጠት፣ በተሽከርካሪ ምርመራ ጉድለት፣ በአሽከርካሪ ብቃት ችግር፣ ባልተፈቀደ ቦታ ማቆም እና ማሽከርከር ምክንያት መኾናቸውን ጠቅሰዋል።
ኅብረተሰቡም የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ሲያደርግ የመንገድ ሕግን አክብሮ እና ጠብቆ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል ብለዋል። በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ የአራተኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት ክፍል ኀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አበባው አየለ በከተማው ራሱን የቻለ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ባለመኖሩ ለከተማዋ የትራፊክ ፍሰት አሉታዊ ጎን እንዳለው ጠቅሰዋል።
አስከፊውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስም በትምህርት ቤቶች፣ ሕዝብ በብዛት እንቅስቃሴ በሚያደርግባቸው ቦታዎች የመንገድ ደኅንነት ትምህርት እየተሰጠ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል።
አሽከርካሪዎች በበኩላቸው የምልክት እና ማመላከቻዎች በውል አለመታየት እና በቂ አለመኾናቸው ለችግሩ መባባስ ምክንያት መኾናቸውን አንስተዋል። የመንገድ ሕግ እና ሥርዓትን ጠብቆ ማሽከርከር ከሁሉም ባለሙያ ይጠበቃልም ብለዋል።
የትራፊክ ፍሰቱን ጤናማ ለማድረግ የሚመለከታቸው የመንግሥት እና የኅብረተሰብ ክፍል በትብብር መሥራት እንደሚገባቸውም ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
