‎የገና እና የጥምቀት በዓላት ለክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

10
ባሕር ዳር: ጥር 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጥር ከሚከበሩ በዓላት መካከል በተለይም የገና እና የጥምቀት በዓል ለአማራ ክልል የቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የክልሉ ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ አስታውቋል።
የቅዱስ ላሊበላ እና አካባቢው አስጎብኝዎች ማኅበር ሥራ አሥፈጻሚ ሻምበል ካሳ ኃይሌ የላሊበላ ከተማ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው በቱሪዝም ላይ የተመሠረተ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ኾኖም ባለፉት ዓመታት በኮሮና፣ በሰሜኑ ጦርነት እና በክልሉ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ተቀዛቅዞ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
‎‌በዚህም አስጎብኝዎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጭዎች ሥራቸው በመቋረጡ ለስደት የተዳረጉ እንዳሉ አንስተዋል፡፡ የገና እና የጥምቀት በዓል በድምቀት መከበሩ ደግሞ ለቱሪዝም እንቅስቃሴው ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል፡፡ ይህም ከተማዋ ወደ ቀድሞ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መመለሷን ያሳየ እና ትልቅ ተስፋ የሰጠ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
‎‌ማኅበረሰቡም በዓሉን ለማክበር የመጣውን ቱሪስት ተቀብሎ በማስተናገድ እና ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ የመመለስ ጅምሩን በጉጉት እና በጥሩ መስተንግዶ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ አካባቢው ሰላም እንዳልኾነ ለሚያስቡ አካላትም ሰላም መኾኑን ያስገነዘበ ነው ብለዋል፡፡
‎‌የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ የገናን በዓል ማኅበረሰቡ በጉጉት የሚጠብቀው የዓመት ልብሱን እና ጉርሱን የሚሸምትበት በዓል ነው ብለዋል፡፡ ሆቴሎች በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት የሚሰጡበት፣ አስጎብኝዎች፣ የስጦታ እቃ ሻጮች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጭዎች በተሻለ የሚንቀሳቀሱበት መኾኑን ነው የገለጹት፡፡
‎‌የዘንድሮው የገና እና የጥምቀት በዓል በርካታ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ታድመውበታል ብለዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የታደሙት 623 የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ሲኾኑ በዘንድሮው ለበዓላቶቹ ብቻ 1 ሺህ 920 የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እንደጎበኙት ገልጸዋል፡፡
‎ይህም የተቀዛቀዘውን ቱሪዝም ወደነበረበት ለመመለስ እና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት፡፡ ከበዓሉ በኋላ ቁጥሩ ቢቀንስም አሁንም የቱሪስት ፍስሰቱ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
‎ተዘግተው የነበሩት የቱሪዝም አገልግሎት ሰጭዎች ሁሉ ወደ ሥራ የተመለሱበት እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ አሁን ያለው የዘርፉ መነቃቃት እንዲቀጥል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ማበርከት አለባቸው ነው ያሉት፡፡
‎በአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም የገና እና የጥምቀት በዓል በክልሉ በድምቀት መከበሩ ካለፉት ዓመታት የተሻለ ሰፊ ቁጥር ያለው ቱሪስት ወደ ክልሉ እንዲመጣ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
‎‌በተለይም ላሊበላ እና ጎንደር በርካታ ቱሪስቶችን አስተናግደዋል። አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም በቂ ዝግጅት በማድረግ ከትንሽ እስከ ትልቅ የንግድ እንቅስቃሴውን አነቃቅቶታል ብለዋል። የበዓሉ መከበር ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በተጨማሪ የክልሉን ገጽታ በመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ ነበረው ነው ያሉት።
‎ባለፉት ስድስት ወራት 24 ሺህ 913 የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ክልሉን የጎበኙት ሲኾን ከዚህም 121 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል።
የሀገር ውስጥ ቱሪስት ፍሰቱም ከ10 ሚሊዮን በላይ ጎብኝ ሲኾን ከዚህም ከ7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል። ለቱሪስት ፍስሰት እና ገቢው ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ በዓላት ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸውም ተናግረዋል።
‎‌ለቱሪዝም ሰላም ወሳኝ ጉዳይ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ክብረ በዓላቶቹ በስኬት መጠናቀቃቸው ክልሉ ሰላም የሰፈነበት እና ለጎብኝዎች የተመቸ መኾኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል።
‎‌ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ከትግራይ ሕዝብ ጋር ትናንትም ዛሬም ነገም ግጭት የለንም” ሰልፈኞች
Next articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት ስብሰባውን ያካሂዳል።