
ደባርቅ: ጥር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት እና አፍሪካን ዋይልድ ፋውንዴሽን በመተባበር በፓርኩ ዙሪያ ለሚገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቅድመ እሳት መከላከል ሥልጠና ሰጥተዋል።
ሥልጠናው በበጋ ወቅት ሊፈጠር የሚችል የእሳት አደጋን ቀድሞ ለመከላከል እና የፓርኩን ሁለንተናዊ ደኅንነት ለማስጠበቅ ያለመ መኾኑ ተገልጿል።
ከፓርኩ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያትተው የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በአምስት ወረዳዎች እና በአንድ ከተማ አሥተዳደር በጥቅሉ በ42 ቀበሌዎች ይዋሰናል።
ፓርኩ በ1958 ዓ.ም በ136 ኪሎ ሜትር ስኩዬር የቦታ ስፋት በመከለል በሀገሪቱ ከተቋቋሙት ሁለት ፓርኮች መካከል አንዱ ነው።
በ1961 ዓ.ም በነጋሪት ጋዜጣ የፓርኩ ማቋቋሚያ አዋጅ ታውጆ በ1970 ዓ.ም በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ በሀገራችን የመጀመሪያ ፓርክ ነው።
በአሁኑ ወቅት ፓርኩ ከ412 ኪሎ ሜትር ስኩዬር በላይ ስፋት ያለው ሲኾን በውስጡ 1 ሺህ 300 የእጽዋት አይነቶች ይገኙበታል። በተጨማሪም ከ36 በላይ የእንስሳት ዝርያዎች የሚገኙ ሲኾን ከነዚህም ውስጥ አራቱ በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ሲገኙ አንዱ ግን በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ብቻ ተወስኖ ይገኛል።
የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከተጋረጡበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመከላከል እና ህልውናውን ጠብቆ እንዲቀጥል ለማስቻል የተለያዩ ተግባራት እየተከናዎኑ እንደሚገኝ የፓርኩ የሥነ ምኅዳር ክትትል እና ማበልጸግ የሥራ ክፍል ኀላፊ ኤፍሬም ወንዴ ይገልጻሉ።
በፓርኩ የእሳት አደጋ እንዳይከሰት እና ሲከሰትም በቀላሉ እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል የሚያሳይ የተቀናጀ ሥልጠና በፓርኩ አዋሳኝ የኾኑ ወረዳዎች ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች መሰጠቱን አንስተዋል።
በተሠሩ የቅድመ መከላከል ሥራዎችም ከ2011 ዓ.ም ወዲህ አመርቂ ለውጥ መታየቱንም አክለዋል።
በአፍሪካን ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የኅብረተሰብ ተጠቃሚነት እና ተሳትፎ ከፍተኛ ባለሙያ ለማ ኤፍሬም ከዚህ ቀደም ያልተደራጀ እና ያልተማከለ የእሳት አደጋ ቡድን ባለመኖሩ የእሳት አደጋ ሲነሳ ከፍተኛ ጉዳት ያደርስ እንደነበር ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት የቅድመ እሳት መከላከል ቡድን በማቋቋም ላለፉት ሦስት ዓመታት ችግሩን ለመቅረፍ ሲሠሩ መቆየታቸውንም አክለዋል።
ከተቋቋመው ቡድን በተጨማሪም ለአካባቢው ማኅበረሰብ በጉዳዩ ዙሪያ በቂ የግንዛቤ ሥልጠና የመስጠት ተግባራት መከናዎናቸውን ገልጸው በዚህም ለውጥ መገኘቱን ጠቅሰዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎችም ወቅቱ በጋ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችልን የእሳት አደጋ ለመቀነስ የተቀናጀ የቅድመ እሳት መከላከል ሥልጠና መሰጠቱ ፋይዳው የጎላ እንደኾነ ገልጸዋል።
ከሥልጠናው በመነሳትም የፓርኩን ደኅንነት ለማስጠበቅ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
