የታሪክ ማህደሯ ደብረ ታቦር ከተማ

17
ባሕር ዳር: ጥር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት እየሠራ መኾኑን የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ አስታውቋል።
ታሪካዊቷ ደብረ ታቦር ከተማ የሰባት ምዕተ ዓመት ገደማ ዕድሜ እንዳላት ይነገራል። ደብረ ታቦር የሚለው ቃል የብርሃን ተራራ እንደማለት እንደኾነም ነው የሚገለጸው።
ከተማዋ ካላት ፖለቲካዊ እና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አኳያ ባለፉት ነገሥታት እንድትመረጥ አድርጓት ቆይቷል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የቱሪዝም ባለሙያ ፈንታ አወቀ ደብረ ታቦር እና አካባቢው የጎብኝዎችን ትኩረት የሚስቡ በርካታ የማይዳሰሱ እና የሚዳሰሱ ታሪካዊ
ቅርሶች እና ቦታዎች ባለቤት ናት ብለዋል።
በደብረ ታቦር እና አካባቢው ከሚገኙ ታሪካዊ አካባቢዎች ውስጥ አጼ ቴዎድሮስ ጥበብን ያስጀመሩበት የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር አንዱ ነው። የአጼ ሱስንዮስ፣ የአጼ ሰርጸ ድንግል እና የአጼ ዮሐንስ ቤተ መንግሥታት አሻራዎችም ይጠቀሳሉ። ደብረ ታቦር ብርሃን ዘኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱ ብጡል የተወለዱባት ታሪካዊ ከተማም ናት።
ከዚህም ባለፈ በከተማዋ እና በአካባቢው በተለያዩ ዘመናት የተተከሉት ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት እንደሚገኙም ገልጸውልናል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የከተማዋ መለያ የኾነው የደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስትያን ይገኝበታል።
ቤተክርስቲያኑ ልዩ ጥበብ የሚስተዋልበት እና በርካታ ቅርሶች የሚገኙበት መኾኑን ባለሙያዋ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ቀዳሚ ተደርጎ የሚወሰደው የተክሌ አቋቋም ዜማ ማስመስከሪያ መገኛም ናት፡፡
ከዚህም ባለፈ ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር፣ የቅዱስ መርቆርዮስ በዓል እና የፈረስ ጉግሥ ሥነ ሥርዓት በከተማዋ ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ ይገኙበታል።
ደብረ ታቦር ከተማ የቱሪዝም ኮንፈረንስ ማዕከልም እንደነበረች ባለሙያዋ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ በክልሉ የተከሰተውን የሰላም እጦት ተከትሎ ወደ አካባቢው ይመጡ የነበሩ ጎብኝዎች ቁጥር መቀነሱን ጠቁመዋል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ከሃይማኖታዊ በዓላት ጋር ተያይዞ ቱሪዝሙ መነቃቃት ማሳየቱን ገልጸዋል።
መምሪያውም ዘርፉን ለማነቃቃት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። በሀገርህን እወቅ መርሐ ግብር ታሪካዊ ቦታዎች እንዲጎበኙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“ከችግሮች በላይ ኾኖ ለልማት መሥራት ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“ከሕልም ወደ እውነት፡ ኢትዮጵያ የቀጠናዊ ብልፅግና ሞተር እና የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል!”