
ባሕር ዳር፡ ጥር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ራስ አሉላ አባ ነጋ ለወረራ ድንበር ጥሶ የመጣውን የጣሊያን ጦር ዶጋሊ ላይ ቀድመው ማሸነፍ የቻሉት በዚህ ሳምንት ነበር።
የአሁኗን “ኤርትራን” የዚያን ጊዜዋን ባሕረ ነጋሽ የሚያሥተዳድሩት ራስ አሉላ አባ ነጋ እና ሠራዊታቸው የጣሊያን ወራሪ ኃይል ዶጋሊ ላይ ተዋግተው ድል ያደረጉት በ1879 ዓ.ም ነበር፡፡
በወቅቱ የራስ አሉላ ሠራዊት ከበባውን አጥቦ ጣሊያኖቹን አጣደፋቸው፡፡ ጣሊያኖቹ አልቻሉም፡፡ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ቢታጠቁም የውጊያ ስልት የሚያውቁትን እና የጦር ልምድ ያላቸውን የራስ አሉላ ሠራዊት ስልት ሊቋቋሙት አልቻሉም፡፡
አዛዡ ኮሎኔል ክሪስቶፎር መሸነፉ ግድ ኾነ። ራስ አሉላ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀውን የአውሮፓ ሠራዊት ድል አደረጉ።
ምንጭ፦ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ” በተክለጻዲቅ መኩሪያ
አጼ ኃይለ ሥላሴ የክብር የፊልድ ማርሻል ማዕረግን ያገኙት ጥር 18/1957 ዓ.ም ነበር። ማዕረጉ የተሰጣቸው የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ ዳግማዊት በኢትዮጵያ ያደረጉትን ታሪካዊ ጉብኝት ተከትሎ ነው።
ማዕረጉን የሰጡት ንግሥት ኤልሳቤጥ ዳግማዊት ሲኾኑ ይህ ስጦታ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጥብቅ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመግለጽ የተደረገ ነው።
ማዕረጉ “የክብር” መኾኑ ንጉሠ ነገሥቱ በእንግሊዝ ጦር ውስጥ ቀጥተኛ ወታደራዊ ዕዝ እንዲኖራቸው አያደርግም።
ንግሥቲቱ ለማዕረጉ መገለጫ የሚኾን የወርቅ ዘንግ ስጦታም አበርክተውላቸዋል።
ምንጭ፦ “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” ሁለተኛ መጽሐፍ በአጼ ኃይለ ሥላሴ የተጻፈ።
የአማርኛ ቋንቋ በዊኪፒዲያ በይፋ የተጀመረው ጥር 1996 ዓ.ም ነው። ይህ ማለት የአማርኛ ዊኪፒዲያ በዓለም ላይ ካሉ ቀዳሚ የዊኪፒዲያ ስሪቶች አንዱ እንዲኾን አስችሎታል።
ዊኪፒዲያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2001 ከተጀመረ ከዓመት በኋላ በፈቃደኛ ግለሰቦች አማካኝነት የአማርኛ ቋንቋ ስሪት እንዲኖር ጥያቄ ቀረበ።
መጀመሪያ ላይ የተወሰኑ የውጭ ሀገር ዜጎች እና ጥቂት ኢትዮጵያውያን “Ethiopia” የሚለውን እና ሌሎች ጥቂት ቃላትን ወደ አማርኛ በመተርጎም ነበር የጀመሩት።
በምስጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
