ተቋርጦ የቆየው የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጄክት በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ ወደ ግንባታ ይመለሳል።

20
ፍኖተ ሰላም፡ ጥር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከማንኩሳ – ብርሸለቆ – 145 ቀበሌ የተቋረጠው የአስፋልት መንገድ ፕሮጄክት ችግሮቹ ተቀርፈው ወደ ሥራ እንዲመለስ የአካባቢው ነዋሪዎች ጠይቀዋል።
ፕሮጄክቱ በ2013 ዓ.ም ቴክስ ኮንስትራክሽን ከተባለ ጠቅላላ የሥራ ተቋራጭ ጋር ውል ተወስዶ ወደ ሥራ ተገብቶ ነበር።
የአስፋልት መንገድ ፕሮጄክቱ በሦስት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ ቢጀመርም በፋይናንስ አቅርቦት እና እንደ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሥራው ቆሞ ቆይቷል።
መንገዱ ቢጠናቀቅ በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የግብርና ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት እና ለማኅበራዊ መስተጋብር ፋይዳው የጎላ እንደሚኾን ነዋሪዎች ተናግረዋል። የሚመለከተው አካል ትኩረት በመስጠት የመንገድ ፕሮጄክቱ ወደ ግንባታ እንዲመለስ እና እንዲጠናቀቅም ጠይቀዋል።
የጃቢ ጠህናን ወረዳ ምክትል አሥተዳዳሪ የቻለ ይርጋ
የአስፋልት ፕሮጄክቱ ሲጠናቀቅ በአካባቢው የተሰማሩ ባለሃብቶች እና አርሶ አደሮች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር መኾኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ ግን ፕሮጀክቱ በመቋረጡ የቅሬታ ምንጭ ኾኗል ነው ያሉት።
ፕሮጄክቱ በሚከናወንበት አካባቢ ላሉ በርካታ አርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ መፈፀሙን እና ለቀሪዎች ደግሞ እንዲከፈላቸው እየተሠራ መኾኑንም አስረድተዋል።
ተቋራጩ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ አቋርጦ በመውጣቱ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቱ መቋረጡን ተናግረዋል። የወረዳ አሥተዳደሩ ለሥራው እንቅፋት የሚኾኑ ነገሮችን እየፈታ፣ ለፕሮጄክቱ እንደገና መጀመርም ምቹ ኹኔታዎችን እየፈጠረ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የቡሬ እና አካባቢው የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሁሉ ዓለምነህ የማንኩሳ – ብርሸለቆ – 145 ቀበሌ የአስፋልት መንገድ ፕሮጄክት አፈፃፀሙ 36 በመቶ ላይ ደርሶ እንደነበር ገልጸዋል።
ግንባታውን ለማስቀጠል የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መጠናቀቃቸውን አረጋግጠዋል። በቀጣይ በአንድ ወር ውስጥ የፕሮጄክቱ ግንባታ ይቀጥላል ብለዋል።
አስፋልት መንገድ ፕሮጀክቱ በ970 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚገነባ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleባለሃብቶች ገብተው እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next article“የሸበሌ ሪዞርት የምሥራቅ ኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ትልቅ አቅም ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ