
ባሕር ዳር: ጥር 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” በሚል መሪ መልዕክት የጎዳና ላይ ትርኢት አካሂዷል።
ባለፉት ዓመታት በተከሰተው ግጭት ከተጎዱ ዘርፎች ውስጥ አንዱ የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንደነበር የተናገሩት የከተማዋ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ አሥራት መሰለ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት በከተማ አሥተዳደሩ በሰላም እጦት ምክንያት የለቀቁ እና ሥራ ያቆሙ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ነው የገለጹት። ይሁን እንጅ ባለፉት ወራት በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ተጀምረው የቆሙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ተግባር እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
በግማሽ ዓመቱ ግንባታቸው ተቋርጠው ከነበሩት ውስጥ ዘጠኝ ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ መግባታቸውን ለአብነት አንስተዋል። አንድ ፕሮጀክትም ወደ ማምረት መግባቱን ጠቅሰዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ለኢንቨስትመንት ምቹ እና ብዙ ጸጋዎች ያሉት መኾኑን ያነሱት ኀላፊው ባለሃብቶች ገብተው እንዲያለሙ ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ባለሃብቶች ገብተው እንዲያለሙም ጥሪ አቅርበዋል።
ማኅበረሰቡም ኢንቨስትመንት ለአንድ አካባቢ መነቃቃት ያለውን ድርሻ በመረዳት የተጀመረው ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው ባለቤት ኾኖ እንዲሠራ ጠይቀዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪዋ ብዙአየሁ ከተማ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ወደ ሥራ ባለመግባታቸው ብዙ ወጣቶች ሥራ አጥ እንዲኾኑ አድርጓል ብለዋል። በአካባቢው ላይም የንግድ እንቅስቃሴ ተዳክሞ መቆየቱን አንስተዋል።
አሁን ላይ በተፈጠረው ሰላም የከተማዋ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ መነቃቃት ማሳየቱን ገልጸዋል።
በሆቴል ሥራ ላይ ተሠማርተው የሚገኙት ሀምሳ አለቃ ዮሐንስ ታደሰ አሁን ላይ በአካባቢው በተፈጠረው ሰላም የንግድ እንቅስቃሴው መነቃቃት ማሳየቱን ገልጸዋል። መንግሥት ለአልሚዎች መሠረተ ልማቶችን እንዲያመቻች እና አሁን የተጀመረውን ሰላም በዘላቂነት ሊያረጋግጥ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
ሌላኛው የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካይ ደሳለኝ ሲራክ የንግድ እንቅስቃሴው ወደ መደበኛ ሥርዓት እንዲመለስ የንግዱ ማኅበረሰብ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
